በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ
የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)ን አዲስ የሙዚቃ አልበም ከማዳመጥ ጋር ተያይዞ ወጣቶች መታሰራቸውን የሚገልጹ መጃዎች ከተለያዩ ምስሎች ጋር ተያይዘው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተሰራጭተዋል፡፡
ብያኔ
ሐሰት ፤ “የጅምላ እስር” ክስተቱን ያሳያሉ ተብለው ከተሰራጩት ምስሎች ከፊሉ ከክስተቱ ጋር ምንም ትይይዝ የሌላቸው እና ከዓመታት በፊት ከተፈጸመ ክስተት የተወሰዱ ሲሆኑ ቀሪው ምስል ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተቀነባበረ መሆኑን MFC አረጋግጧል፡፡
ታዋቂው ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲስ የሙዚቃ አልበም በቅርቡ መለቀቁን ተከትሎ ይህንኑ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በርካታ ሐተታዎች ፣ ክርክሮች እንዲሁም አሳሳች መረጃዎች ጭምር በስፋት ሲሰራጩ እንደነበር MFC ታዝቧል። በተለይም አልበሙ በህዝብ ዘንድ የፈጠረውን ከፍተኛ ትኩረት እና መነጋገሪያነት በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎች እየተሰራጩ ሲሆን ከዚህም መካከል “ሙዚቃውን ያዳመጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለእስር ተዳረጉ” ከሚለው መርጃ ጋር ተያይዘው የተሰራጩት ምስሎች ይገኙበታል፡፡
ከ106 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እና ስንታየሁ ቸኮል የተባለ ግለሰብ በፌስቡክ ገጹ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ ያዳመጡ 105 ሰዎች ታሰሩ የሚልን መረጃን ያጋራ ሲሆን ክስተቱን ለማሳየትም ምስል አብሮ ለጥፏል። ይሁን እንጂ ከሰዓታት በኋላ ምስሉን በሌላ ምስል መቀየሩን በልጥፉ የአርቶዖት ታሪክ (Edit History) MFC ተመልክቷል፡፡ (አርካይቭ እዚህ ይመልከቱ)
በተመሳሳይም ይህንን ይህንን ፣ ይህንን እና ይህንን ጨምሮ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች መረጃውን ከምስሎቹ ጋር አጋርተውት ተመልክተናል፡፡

የማጣራት ሂደት እና ግኝቶች
MFC ከላይ ከቀረቡት መረጃዎች ጋር ተያይዘው የቀረቡት ምስሎች ላይ የማጣራት ስራ አካሂዷል። በዚህም የጎግል ሌንስ መሳሪያን የተጠቀመ ሲሆን በመጀመሪያ መረጃ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል እንደተገለጸው በአዲስ አበባ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ሲያዳምጡ የታሰሩ ሰዎችን አያሳይም።
ምስሉ ከሰባት አመት በፊት መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ/ም በአዲስ አበባ ራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ከከረምቡላ ፣ ጫት እና መጠጥ ቤት የተያዙ ግለሰቦችን የሚያሳይ እንደሆነ MFC አረጋግጧል። ) (እዚህ ይመልከቱ)

ምስል 2: ሁለተኛው መረጃ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል በግልጽ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰራ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችንም MFC ለይቷል፡፡
በምስሉ ላይ በሚታየው የፌደራል ፖሊስ አባል የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ደረት ላይ የሚታየው ጽሑፍ የተዛባ መሆኑ በዕይታ ብቻ አጠራጣሪ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም ምስሉን በጎግል መረጃ አፋላጊ የመረመርን ሲሆን በውጤቱም ይህ ምስል በኢንተርኔት ላይ የቀናት እድሜ ብቻ ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ምርመራችንንም በመቀጠል ፤ ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት AI መሰራት አለመሰራቱን ለማረጋገጥ በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ አውለናል፡፡
1. AI or Not
የሀቅ ማጣራት ቡድናችን ይህንን መሳሪያ በመጠቀም ምስሉን ያጣራ ሲሆን ውጤቱም እንደሚያሳየው ምስሉ በAI የተፈጠረ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

2. Hugging Face AI
በተጨማሪም MFC ይህንን መሳሪያ ጥቅም ላይ በማዋል ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎች የተሰራ የመሆን እድሉ 99.18 ከመቶ መሆኑን አረጋግጦልናል፡፡

ዐውድ
በሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ኢቶሪካ” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበም በይፋ ተለቀቀ። አልበሙ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የቀረበ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና ትኩረትን አግኝቷል። በተለይም “ዳስ ጣል” የተሰኘው ዘፈን በውስጡ “ይዞታል” ከተባለው “ፖለቲካዊ” መልዕክት ብዙ አብዛኛውን ሰዎች ፣ የፖልቲካ ማህበረሰቦች እና ሚዲያዎችን አነጋግሯል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ድምጻዊው አስተጋብቶታል በተባለው የተቃውሞ ይዘት ሳቢያ በገዢው ፓርቲ እና ደጋፊዎቹ እንዳልተወደደ በማህበራዊው ሚዲያ ከሚያሰፍሯቸው መልዕክቶች ማየት ይቻላል፡፡ ሙዚቃው ካስነሳው የፖለቲካ ክርክርና አጀንዳ የተነሳም የተለያዩ ግለሰቦች ለእስር እየተዳረጉ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል የከያኒው የቅርብ ሰዎች የተባሉት ማህሌት ሰለሞን እና ዩሱፍ ያሲን ለእስር መዳረጋቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ በርካቶች ጽፈዋል፡፡
በተጨማሪም ጥቂት ቀናት አስቀድሞም ቁጥራቸው ከ100 የሚልቁ ወጣቶች “የአርቲስቱን ሙዚቃ ተጠቅመው አመጽ ለመቀስቀስ ሞክረዋል” በሚል ለጅምላ እስር መዳረጋቸውን መገናኛ ብዙኅን የዘገቡ ሲሆን ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ 138ቱን ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ያዋላቸው “ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈፀም ታጥቀው በጫካ ከሚንቀሳቀሱ የሽብር እና ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የኢትዮጵያን ሰላም እና ደኅንነት ለማወክ እንዲሁም መጪውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ስምሪት ወስደው ሲንቀሳቀሱ” መሆኑን በመንግስት መገናኛ ብዙኅን አስነግሯል፡፡ ይህ የእስር ሁኔታም እንዚህ ምስሎች እንዲሰራጩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ በተለያዩ ማስረጃዎች እንዳስቀመጥነው ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አልበም መለቀቅ በኃላ ከዘፈኖቹ ጋር “በተያያዘ” ምክንያት አልያም በመንግስት ወገን እንደተገለጸው “ሰላም እና ደኅንነት ለማወክ” በሚል የተለያዩ ግለሰቦች ለእስር የተዳረጉ ቢሆንም ይህንን ክስተት እንደሚያሳይ ተደርገው የተሰራጩት ምስሎች ግን ከፊሉ ከአመታት በፊት በሌላ ክስተት የተነሱ ሲሆኑ ፣ የተቀሩት ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈበረኩ ምስሎች በመሆናቸው ፤ MFC ምስሎቹን ሐሰት ሲል በይኗቸዋል፡፡
