የተጠቀሰው መረጃ
በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ አንድ የመዋለ ሕጻናት (ኬጂ) ተመራቂ ታዳጊ በቅንጡ ተሽከርካሪ ላይ ሆኖ እንደ “ሠርግ” ታጅቦ የሚታይበት ምስል በስፋት ተሰራጭቷል። ምስሉን የአንድ ታዳጊ ልጅ የምርቃት ክብረ በዓል በአደባባይ እንደተከናወነ በማመን ብዙ ተጠቃሚዎች አጋርተውታል።
ብያኔ
በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ ያለው ይህ ምስል እውነተኛ ፎቶግራፍ ሳይሆን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የተቀናበረ መሆኑን የምርመራ ቡድናችን ባደረገው ጥልቅ የማጣራት ስራ አረጋግጧል። በመሆኑም MFC ምስሉን ሐሰት ሲል በይኖታል።
በቅርቡ በፌስቡክ እና በሌሎችም ማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች ላይ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነ አንድ ምስል በስፋት ተዘዋውሯል። ምስሉ አንድ ታዳጊ ልጅ የምርቃት ካባ ለብሶ በዘመናዊ እና ቅንጡ መኪና ጣሪያ ላይ ብቅ ብሎ ረጅም የተሽከርካሪዎች ሰልፍ እየመራ የሚያሳይ ነው።
ይህንኑ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከለጠፉ መካከል በፌስቡክ 209 ሺህ ተከታዮች ያሉት “Finfinne Press John” የተባለ ገጽ ይገኝበታል። ይሄው ገጽ ከምስሉ ጋር አያይዞ “ለአንድ ኬጂ ተማሪ ምርቃት ዋና መንገድ ዘግተው ፣ መኪና ደርድረው ደሴቷን እየናጡ ነው … 120 ቢሊዮን ብር በሚዘረፍበት ሀገር ፣ ፌደራል ፖሊስ ከለላ በሚሰጥበት ደሴት የኬጂ ምርቃት ተራ ነው !!” የሚል ጽሑፍ ለጥፏል።
ምስል 1 ፦ የኬጂ ተመራቂ በዘመናዊ እና ቅንጡ ተሽከርካሪ ላይ እየተጓዘ መሆኑን የሚያሳይ የፌስቡክ ልጥፍ
ይህ መልእክት የህዝብን ሀብት ብክነት ፣ የኑሮ ልዩነትን እና የመንግስት አስተዳደርን የሚተች ይዘት ያለው በመሆኑ በርካታ ተጠቃሚዎች ምስሉን እውነተኛ ክስተት አድርገው በመውሰድ ቁጣቸውን ሲገልጹ እና ሲያጋሩት ታይተዋል። ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስም ይህ ልጥፍ ከ2500 ግብረ መልስ እና 380 አስተያየት በላይ ሲያገኝ ከ180 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።
ምስል 2 ፦ ምስሉ ትክክለኛ እንደሆነ በማመን በልጥፉ ላይ አስተያየት የሰጡ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች
ከዚህ የፌስቡክ ገጽ በተጨማሪም ምስሉ በዚህ ፣ በዚህ ፣ በዚህ ፣ በዚህ እና በዚህ ገጾች ላይም መለጠፉን ልብ ይሏል፡፡
የማጣራት ስራ እና ግኝቶች
MultiFact Check (MFC) ባደረገው ጥልቅ የማጣራት ስራ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ዋና ዋና ማሳያዎችን በማግኘቱ በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወረው ይህ ምስል በትክክል የተነሳ ፎቶግራፍ ሳይሆን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የተቀናበረ መሆኑን አረጋግጧል።
1. የተሽከርካሪው ሰሌዳ ቁጥር መዛባት
በምስሉ ላይ ፊት ለፊት የሚታየው ጥቁሩ ተሽከርካሪ ላይ ያለው ሰሌዳ ቁጥር AA 70707 የፊደላቱ አቀማመጥ ፣ ቅርጽ እና የሰሌዳው ዲዛይን በሀገሪቱ ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው ነባር እንዲሁም አዲሱ ህጋዊ የመኪና ሰሌዳ ጋር ፈጽሞ አይመሳሰልም።
ምስል 3፦ የተሽከርካሪው ሰሌዳ የተዛባ መሆኑን የሚያሳይ
2. የተሽከርካሪዎች ቅርጽ
ከጀርባ የተደረደሩት ነጭ መኪኖች ወደ ኋላ በራቁ ቁጥር ቅርጻቸው እየተበላሸ መብራቶቻቸው እና መስኮቶቻቸው እርስ በርስ እየተደበላለቀ ይሄዳል።
ምስል 4 ፦ ከኋላ የሚታዩት ተሽከርካሪዎቹ ቅርጽ መደበኛ አለመሆኑን የሚያሳይ
3. የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስል ማጣሪያ ግኝት
MFC ለማጣራት ባደረገው ሙከራ የምስሎችን እውነተኛነት ለመለየት በሚያገለግለው Hive Moderation የተባለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስል ማጣሪያ መሳሪያ በመጠቀም ምስሉን መርምሯል። በውጤቱም፣ ምስሉ 98.7% በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተቀናበረ መሆኑን አረጋግጧል። ይህም ማለት ምስሉ በጣም ከፍተኛ የሆነ የAI ይዘት እንዳለው ያሳያል።
ምስል 5 ፦ በAI የተሰሩ ምስሎችን መለያ መሳሪያ የተገኘ ውጤት
አውድ
በኢትዮጵያውያን ዜጎች የኑሮ ሁኔታ ፣ በመንግስት ደጋፊዎች የአኗኗር ዘይቤ እና በመንግስት የ“ቱሪዝም ተኮር” ፕሮጀክቶች ዙሪያ በርካታ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለዚህ ትችት ምላሽ ለመስጠትም “ቅንጡ” እና “ብልጭልጭ” ተብለው የሚተቹትን ፕሮጅክት የሚዳስስ ቃለ መጠይቅ በማድረግ በሚዲያዎች እንዲሰራጩ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቦች የኑሮ ልዩነት ፣ መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል እየጠፋ መምጣት ፣ የዋጋ ንረት የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ጠያቄዎች በተለያዩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ፣ ሚዲያዎች እና ተቋማት መነሳታቸው አልቀረም፡፡
ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚዎች መሬት ላይ “አለ” የሚሉትን የከፋ ድህነት ክደው “ብልጽግና መጥቷል” ለሚሉ የመንግስት ደጋፊዎችን “የደሴቲቱ ነዋሪዎች” የሚሉ ቅጽሎች ሲስጧቸውም በማህበራዊው ሚዲያ ይታያል፡፡ እንደ የአለም ባንክ ያሉ ተቋማት ሪፖርት ከሆነም በኢትዮጵያ ያለው የዜጎች ድህነት በ2025 እአአ ወደ 43% እንደሚያድግ የምጣኔ ሃብት ትንበያ አድርገው ነበር፡፡ በመሆኑም ይህም የታዳጊ ልጅ ምስል የተፈጠረው እና በቀላሉ ሊሰራጭና አመኔታን ያገኘው ከዚህ አውድ በመነሳት ነው፡፡
ምስል 6 ፦ የኬጂ ተመራቂ በቅንጡ ተሽከርካሪ ላይ እየተጓዘ መሆኑን እና የታክሲ አገልግሎትን የሚጠባበቀው ሕዝብ ረጅም ሰልፍ ይዞ የሚያሳይ የፌስቡክ ልጥፍ
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀው ይህ ምስል እና አብሮ የቀረበው መልእክት በፀረ-ሙስና እና በፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ስሜታዊ የሆኑ የህዝብ ንግግሮች እየተካሄዱ ባሉበት ወቅት ነው የተሰራጨው። ለአብነት የፌደራል ፖሊስ የ2018 ዓ/ም ዘጠኝ ወራት ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ታዋቂ አርቲስቶች ህብረተሰቡን 78 ቢሊየን ብር እና 134 ሚሊየን ዶላር መዝረፋቸው አስታውቆ ነበር። ይሄ በሪፖርተር ጋዜጣ ታትሞ ከወጣ በኋላ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል። ( እዚህ ይመልከቱ)
የምስሉ ይዘት ከዚህ ቀድሞ ህብረተሰቡ በመንግስት አስተዳደር ላይ ካለው ቅሬታ ጋር ስለተጣጣመ፣ ብዙዎች ምስሉን እውነተኛ አድርገው በመቀበል ያለምንም ጥርጣሬ ማጋራታቸውን ቀጥለዋል። ይህ የሚያሳየው በስሜታዊ ጉዳዮች ላይ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዴት በፍጥነት ተቀባይነት ሊያገኙ እንደሚችሉ እና የህዝቡን አመለካከት በመቅረጽ ረገድ ያላቸውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳያል።
ማጠቃለያ
በዚህ የማጣራት ስራ ላይ በተደረጉት ጥልቅ ምርመራዎች በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ ያለው በቅንጡ ተሽከርካሪ ታጅቦ የሚታየው የመዋለ ሕጻናት ተመራቂ ምስል እውነተኛ ፎቶግራፍ ሳይሆን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የተቀናበረ መሆኑ በተለያዩ ማሳያዎች ተረጋግጧል። የተሽከርካሪው ሰሌዳ ቁጥር አጻጻፍ እና ንድፍ ህጋዊ ከሆነው የሀገሪቱ የመኪና ሰሌዳ ጋር አለመመሳሰሉ፣ ከጀርባ የተደረደሩት ተሽከርካሪዎች ቅርጽ እና ዝርዝሮቻቸው እርስ በርስ መደባለቃቸው፣ እንዲሁም Hive Moderation በተባለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምስል ማጣሪያ መሳሪያ 98.7 በመቶ በAI የተቀናበረ መሆኑ መረጋገጡ ምስሉ ሙሉ በሙሉ ሐሰተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። በመሆኑም፣ ይህ “ለአንድ ኬጂ ተማሪ ምርቃት የተዘጋ መንገድ” በሚል የተሰራጨው እና አትኩሮት ያገኘው ምስል ሙሉ በሙሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተቀናበረ እንጂ እውነተኛ አይደለም ሲል MFC አረጋግጧል።
የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማንኛውንም መረጃ ከማጋራታቸው እና ከማመናቸው በፊት በተለይም ስሜትን በሚነኩ ምስሎች እና ጽሁፎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ታማኝ የዜና ምንጮች እና እንደ MFC ያሉ መረጃ አረጋጋጮች የሚያወጧቸውን ማብራሪያዎች መከታተል እንዲሁም በምስሎች ላይ ሊታዩ የሚችሉ የAI ምልክቶችን ማለትም የተዛቡ ጽሁፎች ፣ ያልተስተካከሉ የሰውነት አካላት እና ትክክለኛ ያልሆኑ አርማዎች ማስተዋል የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
