በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ
በአማራ ክልል መንግስት እና የፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተፈረመ ስምምነት ላይ ሁለት የውጪ ሃገር ዜጎች ተገኝተዋል። እነሱም “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል ብልጽግና ከሆቴል ለምኖ ያመጣቸው ናቸው፤ ስለጦርነቱ አያውቁም” ተብሎ ከምስል ጋር በፌስቡክ ተሰራጭቷል።
ብያኔ
MFC በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ኃላፊዎች መሆናቸውን በማረጋገጥ መረጃውን ሐሰት ሲል በይኖታል
የማጣራት ስራ እና ግኝቶቹ
በአማራ ክልል የጦር መሳሪያ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አንጃዎች መካከል በማስረሻ ሰጤ የሚመራው ክንፍ ከአማራ ክልልዊ መንግስት ጋር እርቀ ሰላም መፈጸሙ ተዘግቧል። ይህንን ተከትሎ ከ126 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “ፊንፊኔ ፕረስ” የተባለ የፌስቡክ ገጽ አንድ ፎቶ ስለ ስምምነቱ ከሚያብራራ ጽሑፍ ጋር አጋርቷል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎበታል ታዝቧል እንዲባል” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅመዋል። እንዲሁም “ከአንድ ሆቴል ሁለት ነጭ ሴቶችን ለምኖ በማምጣት የድርድሩ ወላጆች አድርጎ በፎቶ እያሳየን ነው” ከሚለው ጽሑፍ ጋር ምስሉን ለጥፎታል (እዚህ ይመልከቱ)።

በአማራ ክልላዊ መንግስትና በማስረሻ ሰጤ መካከል የተደረገው ስምምነት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተዘግቧል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ከላይ የተገለጹት የውጪ ዜጎች የሚታዩበት ምስል በተደጋጋሚ ተጋርቷል። (የኢቢሲ እና ፋና ዘገባዎች ላይ ያሉ ምስሎችን እዚህ፣ እዚህ እና እዚህ ይመልከቱ)።
MFC በስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የሚታዩት የውጪ ሃገር ዜጎች ማን ናቸው? የሚለውን መነሻ በመያዝ በቀረበው መረጃ ላይ የማጣራት ስራ አካሂዷል።

የግለሰቦቹን ማንነት ለማጣራት የ Facecheck ID እና የ ጉግል ሌንስ ምስል ማጣሪያ መሳሪያዎችን ተጠቅመናል። በዚህም የፌስቡክ ገጹ በተጠቀመው ፎቶ ላይ የሚታዩትና ከላይ በምስል 2 ቁጥር 1 እና 2 በሚል ለማሳያነት የተወከሉት ግለሰቦች ማንነት ተረጋግጧል።
ሀ. በቁጥር 1 ላይ የሚታዩት ማን ናቸው?
MultiFact Check (MFC) የ Facecheck ID መሳሪያ በመጠቀም በቁጥር 1 የተወከሉትን ግለሰብ ማንነት ለይቷል። በዚህም በምስሉ ላይ የሚታዩት ግለሰብ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊክ መሆናቸው አረጋግጧል። (እዚህ ይመልከቱ)

የአልጄሪያ ዜግነት ያላቸው ሰልማ ማሊክ ከየካቲት 7 ቀን 2017 (February 15, 2025) ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር በመሆን እየሰሩ ይገኛል።
ምክትል ሊቀ መንበሯ ህዳር 25 ቀን 2018 የተደረገውን የአማራ ክልል መንግስት እና በማስረሻ ሰጤ የሚመራውን የክልሉ ታጣቂ ቡድን ስምምነትን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት የለጠፈውን መረጃ በይፋዊ “X” ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። (እዚህ ይመልከቱ)
ለ. በቁጥር 2 ላይ የሚታዩት ማን ናቸው?
“ፊንፊኔ ፕረስ” የተባለው የፌስቡክ ገጽ በለጠፈው ፎቶ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊክ አጠገብ ሁለተኛዋ ግለሰብ ይታያሉ። የግለሰቧን ማንነት ለማረጋገጥ MFC የFacecheck ID መሳሪያን እና የጉግል ሌንስ ምስል መፈለጊያን ተጠቅሟል።

በዚህም ቁጥር 2 በሚል MFC የለያቸው ግለሰብ ፋተን አጋድ ሲሆኑ የአልጄሪያ ተወላጅ የሆኑት እኚህ የአፍሪካ ህብረት ሹም የምክትል ሊቀ መንበሯ የካቢኔ አባል እንደሆኑ አረጋግጠናል። (እዚህ ይመልከቱ)
በተጨማሪም ፋተን አጋድ የአማራ ክልል አስተዳደር እና ታጣቂዎቹን የስምምነት ፊርማ በተመለከተ በ “X” ገጻቸው ያጋሩት መረጃ እዚህ ይገኛል።
አውድ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የፌደራል መንግስት በ2015 ታጣቂ ኃይሎችን ከመከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ ውጪ በፌደራል የጸጥታ መዋቀር እንዲካተቱ ውሳኔ አድርገዋል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው።
በክልሉ ፋኖ በሚል ጥቅል ስያሜ በሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ጎጃም የተደራጁ ታጣቂዎች ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት ለአመታት እየተዋጉ ይገኛል።
በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልል ውስጥ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ፋኖ በሚል መጠሪያ በሚንቀሳቀሱ በእነዚህ የተለያዩ አንጃዎች መካከል ለአመታት የዘለቀውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት የሰላም ምክር ቤት ተቋቁሞ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይሄው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
መንግስትን ከ”ፋኖ” ታጣቂዎች ጋር ለማደራደር የተቋቋመው ምክር ቤት ታጣቂዎቹ በተለያየ አደረጃጀት ስር መሆናቸው ድርድር ለማድረግ ምቹ እንዳልሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።
ህዳር 25 ቀን 2018 የክልሉ መንግስት የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር በይፋ የሰላም ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ በክልሉ ፕሬዝዳንት አረጋ ከበደ እና የታጣቂ ቡድኑ መሪ በሆነው ማስረሻ ሰጤ በኩል ነው የተፈጸመው።
መደምደሚያ
በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በቀን በቀን እየጨመረ ነው። በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዕድገት የጽሑፍ፣ ድምጽ፣ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ውስብስብና እውነተኛ መረጃን ከሐሰት ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎታል።
በመሆኑም MFC ሁሉንም ግኝቶች ከገመገመ በኋላ፣ በምስሉ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል ብልጽግና ከሆቴል ለምኖ ያመጣቸው ናቸው” በሚል በፌስቡክ ገጹ የተላለፈው መረጃ ሐሰት ነው በማለት በይኖታል።
ስለዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች እና ተጠቃሚዎች ስለሚያጋሯቸው መረጃዎች አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እንዲያደርጉ MFC ያሳስባል።
