በመንግስት እና ፋኖ ስምምነት ወቅት የታዩት የውጪ ዜጎች ማን ናቸው?

በፋሲል አረጋይ

የተጠቀሰው መረጃ

በአማራ ክልል መንግስት እና የፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተፈረመ ስምምነት ላይ ሁለት የውጪ ሃገር ዜጎች ተገኝተዋል። እነሱም “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል ብልጽግና ከሆቴል ለምኖ ያመጣቸው ናቸው፤ ስለጦርነቱ አያውቁም” ተብሎ ከምስል ጋር በፌስቡክ ተሰራጭቷል።

ብያኔ

MFC በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ኃላፊዎች መሆናቸውን በማረጋገጥ መረጃውን ሐሰት ሲል በይኖታል

የማጣራት ስራ እና ግኝቶቹ

በአማራ ክልል የጦር መሳሪያ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አንጃዎች መካከል በማስረሻ ሰጤ የሚመራው ክንፍ ከአማራ ክልልዊ መንግስት ጋር እርቀ ሰላም መፈጸሙ ተዘግቧል። ይህንን ተከትሎ ከ126 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “ፊንፊኔ ፕረስ” የተባለ የፌስቡክ ገጽ አንድ ፎቶ ስለ ስምምነቱ ከሚያብራራ ጽሑፍ ጋር አጋርቷል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎበታል ታዝቧል እንዲባል” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅመዋል። እንዲሁም “ከአንድ ሆቴል ሁለት ነጭ ሴቶችን ለምኖ በማምጣት የድርድሩ ወላጆች አድርጎ በፎቶ እያሳየን ነው” ከሚለው ጽሑፍ ጋር ምስሉን ለጥፎታል (እዚህ ይመልከቱ)።

ምስል 1

በአማራ ክልላዊ መንግስትና በማስረሻ ሰጤ መካከል የተደረገው ስምምነት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተዘግቧል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ከላይ የተገለጹት የውጪ ዜጎች የሚታዩበት ምስል በተደጋጋሚ ተጋርቷል። (የኢቢሲ እና ፋና ዘገባዎች ላይ ያሉ ምስሎችን እዚህእዚህ እና እዚህ ይመልከቱ)።

MFC በስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የሚታዩት የውጪ ሃገር ዜጎች ማን ናቸው? የሚለውን መነሻ በመያዝ በቀረበው መረጃ ላይ የማጣራት ስራ አካሂዷል።

ምስል 2

የግለሰቦቹን ማንነት ለማጣራት የ Facecheck ID እና የ ጉግል ሌንስ ምስል ማጣሪያ መሳሪያዎችን ተጠቅመናል። በዚህም የፌስቡክ ገጹ በተጠቀመው ፎቶ ላይ የሚታዩትና ከላይ በምስል 2 ቁጥር 1 እና 2 በሚል ለማሳያነት የተወከሉት ግለሰቦች ማንነት ተረጋግጧል።

ሀ. በቁጥር 1 ላይ የሚታዩት ማን ናቸው?

MultiFact Check (MFC) የ Facecheck  ID መሳሪያ በመጠቀም በቁጥር 1 የተወከሉትን ግለሰብ ማንነት ለይቷል። በዚህም በምስሉ ላይ የሚታዩት ግለሰብ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊክ መሆናቸው አረጋግጧል። (እዚህ ይመልከቱ)

የአልጄሪያ ዜግነት ያላቸው ሰልማ ማሊክ ከየካቲት 7 ቀን 2017 (February 15, 2025) ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር በመሆን እየሰሩ ይገኛል።

ምክትል ሊቀ መንበሯ ህዳር 25 ቀን 2018 የተደረገውን የአማራ ክልል መንግስት እና በማስረሻ ሰጤ የሚመራውን የክልሉ ታጣቂ ቡድን ስምምነትን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት የለጠፈውን መረጃ በይፋዊ “X” ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። (እዚህ ይመልከቱ)

ለ. በቁጥር 2 ላይ የሚታዩት ማን ናቸው?

“ፊንፊኔ ፕረስ” የተባለው የፌስቡክ ገጽ በለጠፈው ፎቶ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊክ አጠገብ ሁለተኛዋ ግለሰብ ይታያሉ። የግለሰቧን ማንነት ለማረጋገጥ MFC የFacecheck ID መሳሪያን እና የጉግል ሌንስ ምስል መፈለጊያን ተጠቅሟል።

በዚህም ቁጥር 2 በሚል MFC የለያቸው ግለሰብ ፋተን አጋድ ሲሆኑ የአልጄሪያ ተወላጅ የሆኑት እኚህ የአፍሪካ ህብረት ሹም የምክትል ሊቀ መንበሯ የካቢኔ አባል እንደሆኑ አረጋግጠናል። (እዚህ ይመልከቱ)

በተጨማሪም ፋተን አጋድ  የአማራ ክልል አስተዳደር እና ታጣቂዎቹን የስምምነት ፊርማ በተመለከተ በ “X” ገጻቸው ያጋሩት መረጃ እዚህ ይገኛል።

አውድ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የፌደራል መንግስት በ2015 ታጣቂ ኃይሎችን ከመከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ ውጪ በፌደራል የጸጥታ መዋቀር እንዲካተቱ ውሳኔ አድርገዋል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው።

በክልሉ ፋኖ በሚል ጥቅል ስያሜ በሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ጎጃም የተደራጁ ታጣቂዎች ከፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት ለአመታት እየተዋጉ ይገኛል።

በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልል ውስጥ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ፋኖ በሚል መጠሪያ በሚንቀሳቀሱ በእነዚህ የተለያዩ አንጃዎች መካከል ለአመታት የዘለቀውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት የሰላም ምክር ቤት ተቋቁሞ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይሄው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።

መንግስትን ከ”ፋኖ” ታጣቂዎች ጋር ለማደራደር የተቋቋመው ምክር ቤት ታጣቂዎቹ በተለያየ አደረጃጀት ስር መሆናቸው ድርድር ለማድረግ ምቹ እንዳልሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።

ህዳር 25 ቀን 2018 የክልሉ መንግስት የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር በይፋ የሰላም ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ በክልሉ ፕሬዝዳንት አረጋ ከበደ እና የታጣቂ ቡድኑ መሪ በሆነው ማስረሻ ሰጤ በኩል ነው የተፈጸመው።

መደምደሚያ

በማህበራዊ ሚዲያ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በቀን በቀን እየጨመረ ነው። በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዕድገት የጽሑፍ፣ ድምጽ፣ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ውስብስብና እውነተኛ መረጃን ከሐሰት ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎታል።

በመሆኑም MFC ሁሉንም ግኝቶች ከገመገመ በኋላ፣ በምስሉ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች “ድርድሩ የእውነት እንዲመስል ብልጽግና ከሆቴል ለምኖ ያመጣቸው ናቸው” በሚል በፌስቡክ ገጹ የተላለፈው መረጃ ሐሰት ነው በማለት በይኖታል።

ስለዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች እና ተጠቃሚዎች ስለሚያጋሯቸው መረጃዎች አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እንዲያደርጉ MFC ያሳስባል።

We at the MFC strive to verify misleading and false claims so that people get fact-based information and make an informed decision as well. In the process of our work, accuracy and transparency hold a central role. Therefore, if you see errors in our content, please write to us at info@multifactcheck.org so that our team will make corrections.

Share post on Social media

See related posts

የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)ን አዲስ የሙዚቃ አልበም ከማዳመጥ ጋር ተያይዞ ወጣቶች መታሰራቸውን የሚገልጹ መጃዎች

ABOUT MFC

MultiFactCheck

(MFC) is an independent fact-checking organization which is launched to pin-point, track-down, scrutinize, investigate, interrogate, publish and distribute the factual accuracy of claims made by public figures. MFC’s project has geographical priorities. Our work mainly focuses on nations in the Horn of Africa and their diaspora community who reside abroad. We operates from various regions of Africa, Europe and North America. Through a multitude of professional proficiency, MFC deploys best practices of journalism, scholarship and expertise in order to flag, investigate and publish a fact.