በናኦል ጌታቸው
የተጠቀሰው መረጃ: Amhara Youth Association (ወይም በአማርኛ የአማራ ወጣቶች ማህበር) የተባለ እና በርካታ ተከታዮች ያሉት የX አካውንት “ዘመቻ ውባንተ” በአዲስ አበባ መጀመሩን ከቪዲዮ ጋር ትዊት አድርጓል።
ብያኔ: የተለጠፈው ቪዲዮ የቆየ እና ከአሁኑ የአማራ ክልል ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሐሰት ነው።
Amhara Youth Association (ወይም በአማርኛ የአማራ ወጣቶች ማህበር) የሚል ስም ያለውና ከ 36,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የX አካውንት, አዲስ አበባ “ዘመቻ ውባንተ” እየተባለ የሚጠራን የውጊያ ዘመቻ መቀላቀሉን የያዘ ትዊት ቪዲዮ አያይዞ በመጋቢት 13/2016 አጋርቷል። ይህም ልጥፍ ይህ ፅሁፍ እስከሚታተምበት ዕለት ድረስ ከ 25,000 በላይ ዕይታ ያገኘ ሲሆን ከ110 ጊዜ በላይም በድጋሚ ተጋርቷል።
ከቪዲዮው ጋር የተያያዘው ፅሑፍም እንዲህ ይነበባል። “ዘመቻ ውብአንተ በአዲስ አበባ ተጀመረ! በመጨረሻም ቢሆን የፒያሳ ወጣቶች ከእንቅልፋቸው እየነቁ ነው። ተቃውሞ እየተቀጣጠለ ነው። አንድ ባለስልጣናት የሚንቀሳቀሱበት አውቶቡስ ላይ የቦንብ ጥቃት መድረሱን አረጋግጠናል”
ይሁን እንጂ ፤ (MultiFactCheck (MFC) የተጠቀሰውን መረጃ እውነተኝነት Fake news debunker by InVID & WeVerifyን በመጠቀም አጣርቷል። ውጤቱም እንደሚያሳየው ቪዲዮው መስከረም 4/2011 ዓ.ም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ወደሐገር ውስጥ በሚመለሱበት ወቅት “ቄሮ” እየተባሉ በሚጠሩ የኦሮሞ ወጣቶችና በአዲስ አበባ ወጣቶች መሐከል የተፈጠረውን ግጭት ከሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ሲሆን ፤ በትዊተር ላይ እንደተሰራጨው በዚህ ጊዜ ከሚካሄደው የአማራ ክልል ግጭት ጋር የሚያያዝ አይደለም።
ከአምስት አመት በፊት የነበረን ክስተት የሚያሳየው ይህ ቪዲዮ በዕለቱ መስከረም 4/2011 ዓ.ም ፌስቡክን (ይህንን መስፈንጠሪያ ይመልከቱ ) እና ዩቲዩብን (ይህንን መስፈንጠሪያ ይመልከቱ) ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ ነበር።
በመሆኑም ፤ MFC የተጠቀሰው መረጃ ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል።
አውድ
የአማራ ክልል ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ በግጭትና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ይገኛል። በዚህም የመንግስትና ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው በሚጠሩ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ፣ ውብአንተ አባተ የተባለና ከፋኖ ኃይሎች መሪዎች አንዱ የሆነው መገደሉ ሲዘገብ ቆይቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ታጣቂዎቹ በዚሁ መሪያቸው ስም የተሰየመ የውጊያ ዘመቻ መጀመራቸውን በየማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያጋሩ ይስተዋላል። ይህም ከላይ የተጠቀሰው መረጃም በዚህ አውድ ውስጥ የተሰራጨ ነው።