ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗልን?

Thumbnail image for a fact-checked article about re-election claim in Wolayta

በፋሲል አረጋይ

የተጠቀሰው መረጃ

“የህዝብ ድምጽ” የሚል ስያሜ የሚጠቀም አንድ የፌስቡክ ገጽ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም “ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል” የሚል መረጃ ከምስል ጋር አጋርቷል

ብያኔ

ሐሰት፡ MFC ባደረገው የማጣራት ስራ ቦርዱ በወላይታ ዞን በድጋሚ ምርጫ እንደሚካሄድ በመጥቀስ መግለጫ አልሰጠም፡፡

MFC ይህንን የማጣራት ስራ እየሰራ ባለበት ወቅት ልጥፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ1600 በላይ ላይክ እና ከ150 በላይ አስተያየቶችን አግኝቷል። እንዲሁም ለሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ተደራሽ እንዲሆን ከ110 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ይህ ሁኔታ መረጃው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መድረሱን ያሳያል።

መረጃው ከላይ ከተተቀሰው የፌስቡክ ገጽ በተጨማሪ በሌሎች ገጾችም የተሰራጨ ሲሆን ፣ አብዛኞቹም በርካታ ግብረ መልሶችን አግኝተዋል፡፡ (እነዚህን ማስፈንጠሪያዎች ይመልከቱ፦ ማስፈንጠሪያ 1ማስፈንጠሪያ 2 እና ማስፈንጠሪያ  3)

ምስል 1፡ ከፌስቡክ ገጹ የተወሰደ ስክሪንሾት

የማጣራት ሂደት እና ግኝቶች

MFC በፌስቡክ ገጹ የተላለፈውን ይህንን መረጃ ለማጣራት የተለያዩ ሙያዊ መንገዶችን የተከተለ ሲሆን በዚህም የመጀመሪያው የማጣራት ሂደት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕለቱ ጋዜጣዊ ከተተቀሰው ጉዳይ ጋር በተያያዘ መግለጫ መስጠቱን መፈተሽ ነበር።

MFC ከቦርዱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ማረጋገጥ እንደቻለው ቦርዱ ከአንድ ቀን በፊት ማለትም ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 7:30 በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል መግለጫ ለመስጠት ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ምስል 2፡ ከ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” ይፋዊ ፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ስክሪንሾት

MFC በዕለቱ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የፌስቡክ ገጽ በቀጥታ የተላለፈውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ የተመለከተ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በሰጡት 29 ደቂቃ ከ 20 ሴኮንድ ርዝማኔ ባለው መግለጫ ውስጥ “በወላይታ ዞን ጊዜያዊ ውጤት ተሰርዟል በድጋሚ ምርጫ ይደረጋል” የሚል ንግግር አለማድረጋቸውን አረጋግጧል (እዚህ።ይመልከቱ)።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቀጥታ ሳያስተላልፈው በቀረው እና በመግለጫው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች ያቀረቡት ጥያቄ እንዲሁም የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የሰጡት ምላሽ በሚገኝበት የድምጽ ቅጂ ላይም ቦርዱ እንዲህ አይነት ውሳኔ እንዳስተላለፈ የሚገልጽ ይፋዊ መረጃ አልተገኘም።

ከዚህም ባሻገር የትኛውም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቦርዱን ጠቅሰውም ሆነ ሳይጠቅሱ የሰሩት ዘገባ አለመኖሩን MFC የማህበራዊ ሚዲያ ሞኒተሪንግ አጣርቷል፡፡

እነዚህ የፌስቡክ ገጾች መረጃውን ያጋሩት ከምስል ጋር አያይዘው ሲሆን ፤ ምስሉም በትኩረት ላልተመለከተው ሰው የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ የቀጥታ መግለጫ ሲሰጡ እና የመገናኛ ብዙኃንም ሲታደሙ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ምስሉ እውነተኛ ላለመሆኑ በርካታ አጠራጣሪ ምልክቶችን ይዟል፡፡

ምስል 3፡ በፌስቡክ ላይ ከተሳሳተው መረጃ ጋር ሲዘዋወር የነበረው ምስል (አጽንዖት የተጨመረ)

ከላይ በምስሉ ላይ በቀይ ለማመልከት እንደተሞከረው በምስሉ ላይ ማንነቱ የማይታወቅ የሚዲያ መለያ ምልክት (ሎጎ) በስተቀኝ ከላይ ተቀምጦ ይታያል፡፡ መግለጫው የሚሰጥበት አትሮኖስ ላይ የሚታየውና የምርጫ ቦርድ ስምና ምልክትን እንዲያሳይ የታሰበው ክብ ምስላዊ መግለጫም የተሳሳተ ምልክትና አጻጻፍን ይዟል፡፡ በሌላ በኩል በምስሉ ላይ የሚታዩት ጽሑፎች አብዛኞቹ የተሳሳቱ ፣ ከፊሉ ትርጉም የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህም ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመሰራቱ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የምስሉን በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሰራት በሚገባ ለማጽናትም የመረጃ ማጣራት ቡድናችን የተለያዩ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል፡፡ ለማሳያነትም የሁለቱን መሳሪያዎች ውጤት ከዚህ በታች እንደተመላከተው ተቀምጧል፡፡

ምስል 4፡ Fake Image Detector የተሰኘው መሳሪያ ምስሉ 100% በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደተሰራ ሲያመላክት  Huggingface ደግሞ በበኩሉ ምስሉ 84.59% በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደተሰራ አመልክቷል፡፡

አውድ

በአማራ ክልል 8 እንዲሁም በትግራይ ክልል 38 ምርጫ ክልሎች ያልተሳተፉበት 7ኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል። ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተገኘው መረጃ መሰረት በዕለቱ እስከ ምሽት 2 ሰዓት ድረስ ድምጽ የሰጡ መራጮች ቁጥር 40 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን የድምጽ መስጫ ጊዜ ገደቡም እስከ እኩለ ሌሊት 6 ሰዓት ድረስ ተራዝሞ ነበር።

በሌላ በኩል በዕለቱ ባጋጠመ የጸጥታ ችግር ምክንያት በ143 ምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ሳይካሄድ መቅረቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁንና ጊዜያዊ ውጤት የማሳወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል። በተፈናቃዮች እና በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ዛሬ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላም ቦርዱ በቀጣዮቹ ቀናት ይፋዊ ውጤቱን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ማጠቃለያ

በመሆኑም በፌስቡክ ገጾች የቀረበው ምስል የተፈበረከ ተያይዞ የተሰራጨው ዘገባ ማለትም “በወላይታ ዞን በድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል” የሚለው መረጃ ይህ ጹሁፍ እስከሚታተምበት ወቅት ድረስ ሐሰት መሆኑን MFC አረጋግጧል።

እንደ ምርጫ ባሉ ትልልቅ ሀገራዊ ክንውኖችና ክስተቶች ወቅት በርካታ የሀሰተኛ መረጃዎች የሚሰራጩ በመሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መረጃዎችን እያጣሩ እና ከሚመለከተው አካል ገጾች ጋር እያመሳከሩ እንዲተቀሙ MFC አበክሮ ያሳስባል፡፡

We at the MFC strive to verify misleading and false claims so that people get fact-based information and make an informed decision as well. In the process of our work, accuracy and transparency hold a central role. Therefore, if you see errors in our content, please write to us at info@multifactcheck.org so that our team will make corrections.

Share post on Social media

See related posts

በግንቦት 23/ 2019 ዓ.ም የወጣውን 31ኛ እትም ቁጥር 2722 የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ “ነው” በሚል

ABOUT MFC

MultiFactCheck

(MFC) is an independent fact-checking organization which is launched to pin-point, track-down, scrutinize, investigate, interrogate, publish and distribute the factual accuracy of claims made by public figures. MFC’s project has geographical priorities. Our work mainly focuses on nations in the Horn of Africa and their diaspora community who reside abroad. We operates from various regions of Africa, Europe and North America. Through a multitude of professional proficiency, MFC deploys best practices of journalism, scholarship and expertise in order to flag, investigate and publish a fact.