የተጠቀሰው መረጃ
በፌስቡክ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስም እና ፊርማ በመጠቀም የተዘጋጀ አንድ ደብዳቤ በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል። ይህ ደብዳቤ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ክፍያ በተመለከተ እንደሆነ ይገልጻል።
ብያኔ
MFC ባካሄደው ጥልቅ ምርመራ መሰረት፣ ደብዳቤው ሙሉ በሙሉ የተቀነባበረ ሀሰተኛ ሰነድ ሆኖ ተገኝቷል። ምክንያቱም ደብዳቤው የአጻጻፍ ደንቦችን ይጥሳል፤ አድራሻው እና ፈራሚው ወጥነት የላቸውም፤ የመለያ ቁጥሩ፣ ራስጌው፣ ኦፊሴላዊው አርማ አለመኖር እና የቲተር ማህተም የተሳሳተ አቀማመጥ፣ እንዲሁም የርዕሱ እና የይዘቱ አለመጣጣም የሰነዱን ሐሰተኛነት በማሳየት ምንም አይነት ኦፊሴላዊ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጧል።
“የምርጫ አስፈጻሚዎች” የሚል መጠሪያ ያለው የፌስቡክ ገጽ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ/ም ከመራጮች ምዝገባ እስከ ምርጫ ቀን በስራ ላይ የነበሩ አስፈጻሚዎችን ማሳወቂያ እና ማረጋገጫ እንደሆነ የሚገልጽ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ስም እና የቦርዱ “ማህተም” ያለበት ደብዳቤ አሰራጭቷል ። ልጥፉ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ወቅት ከ4100 በላይ ግብረ መልስ እና ከ240 በላይ አስተያየቶች ሲያገኝ 281 ጊዜ ተጋርቷል።
ምስል-1:- ከፌስቡክ ገጹ የተወሰደ የደብዳቤ ምስል (Screenshot)
የማጣራት ስራ እና ግኝቶች
MultiFact Check (MFC) በደብዳቤው ይዘት እና ትክክለኛነት ላይ የማጣራት ስራ ሰርቷል። በዚህም የተገኙ ግኝቶች፡
1. የአድራሻ እና ፈራሚ ቅራኔ
ከዚህ በታች በምስል ላይ እንደምትመለከቱት በግራ የደብዳቤው አናት ላይ “ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” በማለት የተጻፈ ሲሆን ይህ የሚያሳየው ደብዳቤው ከሌላ አካል ወደ ምርጫ ቦርድ የተላከ መሆኑን ነው። ነገር ግን ከታች በፈራሚ ቦታ ላይ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ” የሚል ጽሑፍ እና የቦርዱ “ማህተም” ሰፍሮበታል። ሆኖም አንድ ተቋም ለራሱ ተቋም በዚህ መልኩ ደብዳቤ አድራሻ አድርጎ አይጽፍም። ይህም የደብዳቤ አጻጻፍ ህግጋትን አለማወቅ ያሳያል።
ምስል-2፡- ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተብሎ የተጻፈው ነገር ግን በቦርዱ ሰብሳቢ ስም ፣ ፊርማ እና “ማህተም” መውጣቱን የሚያሳይ
2. የደብዳቤ ይዘት
በደብዳቤው ይዘት ላይ በተደረገ ተጨማሪ የማጣራት ስራ MFC ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የደብዳቤውን ሀሰተኛነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አግኝቷል።
2.1 መለያ ቁጥር አለመኖር፦ ማንኛውም ይፋዊ የመንግስት ወይም የተቋም ደብዳቤ ከቀን በተጨማሪ የራሱ የሆነ መለያ ቁጥር ወይም Reference Number አለው። በዚህ ሰነድ ላይ ግን ከቀን ውጪ ምንም አይነት የደብዳቤ ቁጥር አልሰፈረበትም።
2.2 የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማ አለመኖር፦ ከዚህ በታች በምስል እንደሚታየው ቦርዱ የሚያወጣቸው ይፋዊ ደብዳቤዎች ከላይ በራስጌው ላይ የተቋሙን ትክክለኛ አርማ እና ከታች ሙሉ አድራሻ እንዲሁም በቀኝ በኩል የተቋሙን የማህበራዊ ትስስር ገጽ አድራሻዎች የያዙ ናቸው። ይህ ሰነድ ግን ምንም አይነት ራስጌ ወይም ሄደር የሌለው እና በቀላሉ በነጭ ወረቀት ላይ የተተየበ ነው።
ምስል-3፡- በግራ በኩል ያለው ትክክለኛው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ሲሆን በቀኝ በኩል ያለው በፌስቡክ የተሰራጨው ደብዳቤ ምስል ያሳያል
2.3 የቲተር ማህተም አቀማመጥ፡- ከላይ ባለው ምስል በግልጽ እንደሚታየው በትክክለኛ የቦርዱ ይፋዊ ደብዳቤ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ስም እና ኃላፊነት በቲተር ማህተም የተቀመጠ ነው።
2.4 የደብዳቤው ይዘት እና ርዕስ መለያየት፦ ደብዳቤው በአንድ በኩል “የምርጫ አስፈጻሚዎች ክፍያ” የሚል ርዕስ ቢይዝም በውስጡ ግን ስለ ክፍያ መጠን ፣ የክፍያ ጊዜ ወይም አፈጻጸም የሚያወራው ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ የለም ይልቁንም ንብረት ማስረከብን እና ስራ ላይ መገኘትን ስለማረጋገጥ ብቻ ያትታል። የርዕሱ እና የውስጥ ይዘቱ አለመገናኘት ሌላው የሀሰተኛነቱ ማረጋገጫ ነው።
አውድ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአስፈጻሚነት የተሳተፉ ግለሰቦች የውል ክፍያቸው በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ለከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና መዳረጋቸውን በመግለጽ ቅሬታ ማቅረባቸው ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ/ም ተዘግቧል። እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፣ ከቦርዱ ጋር በተደረገው የስራ ውል መሠረት ለ54 የሥራ ቀናት በቀን 548 ብር ታስቦ በአጠቃላይ 29,592.00 ብር ሊከፈል ስምምነት ተደርጓል።
ይሁን እንጂ አጠቃላይ የምርጫ ሥራው ተጠናቆ የሥራ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በሰነድ በተረከቡ በ15 ቀናት ውስጥ መፈጸም የነበረበት የ60 በመቶ የመጨረሻ ክፍያ (17,755.20 ብር) እስካሁን ሊከፈላቸው አልቻለም። ከዚህም በተጨማሪ የ14 ቀናት የሥራ ክፍያ 7,672 ብር እና የ4 ቀናት የስልጠና አበል 2,192 ብር በደብዳቤ ሊከፈላቸው ቃል ተገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሲሰጡ ” ከምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በነበረው ውል መሰረት የመጀመሪያውን 40% ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከፍሏል። ይህንን ለመክፈል ትልቅ ችግር ገጥሞን የነበረው በሶማሌ ክልል እና አፋር ክልል ነው። አስፈጻሚዎቻችን የባንክ አካውንት ስላልነበራቸው የምርጫ ቦርድ ሰራተኞች በቦታው ተገኝተው ገንዘብ በካሽ አውጥተው መክፈል ነበረባቸው ይህንን አድርገዋል፤ የክፍያ ሂደቱን አጠናቀዋል። ቀሪ 60 በመቶው የሚከፈለው የምርጫ አስፈጻሚዎች ከቦርዱ የተቀበሉትን ንብረት ለቦርዱ ሙሉ ለሙሉ አስረክበው ሲጨርሱ የሚከፈል ይሆናል። ይህንን የማጥራት ሂደት ጀምረናል” ብለዋል። (ምንጭ Tikvah Ethiopia )
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ስም እና “ማህተም” ይዞ በፌስቡክ ገጽ ላይ የተሰራጨው ይህ ደብዳቤ በውስጡ ካለው የአድራሻ እና ፈራሚ ቅራኔ እንዲሁም የይዘት ስህተት አንጻር ሙሉ በሙሉ ሀሰተኛ ነው ሲል MFC በይኖታል።
ዜጎች በተለይም የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲህ አይነት ተቀነባብረው የሚለቀቁ መረጃዎችን ከማመን እና ከማሰራጨት ሊቆጠቡ ይገባል። MFC ትክክለኛ እና ይፋዊ መረጃዎችን ለማግኘት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የተረጋገጡ ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች መጠቀምን ይመክራል።
