በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ
በኢትዮጵያ የሄፓታይተስ ኤ እና ሲ ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ እንደሆነ በመግለጽ የጀበና ቡና ነጋዴዎች እና ተጠቃሚዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚገልጽ መረጃ በቲክቶክ እና ፌስቡክ ገጾች ተሰራጭቷል። ማስጠንቀቂያውም በዋናነት በሽታዎቹ (ሄፓታይተስ ኤ እና ሲ) ሲኒ በመጋራት ፤ ወይም በበሽታዎቹ የተያዘ ሰው ቡና የጠጣበት ሲኒ በሚገባ ካልተቀቀለ እንደሚተላለፍ አጽንዖት የሚሰጥ ነው፡፡
ብያኔ
መረጃው በከፊል ብቻ እውነት ነው፡፡ በሄፓታይተስ ኤ የተጠቃ ሰው የጠጣበትን ሲኒ በሚገባ ሳያጥቡና ሳየቀቅሉ መጠቀም በሽታውን ከታማሚው ወደ ጤነኛው የሚያስተላልፍ ሲሆን ፤ በአንጻሩ ከሄፓታይተስ ሲ ግን ቀጥተኛ የሆነ የደም ንክኪ ከሌለ በቀር ሲኒ በመጋራት ሊተላለፍ እንደሚችል መጠቀሱ ደግሞ ስህተት ነው።
የማጣራት ስራ እና ግኝቶቹ
ከ18ሺህ 500 በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ ገጽ ሄፓታይተስ ኤ እና ሲ (Hepatitis A and C) የተባሉ የጉበት በሽታዎች እየተስፋፉ ነው በሚል ያስተላለፈው መረጃ ከ 1.1 ሚሊዮን በላይ ዕይታዎችን አግኝቷል። (እዚህ ይመልከቱ) በተጨማሪም 311ሺህ ተከታዮች ያሉት “Zena24” የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የጀበና ቡና የምትጠቀሙ ተጠንቀቁ! በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ በማይጠበቅ ሁኔታ የሄፓታይቲስ A እና C ስርጭት እየጨመረ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዜና አጋርቷል። በመረጃው በተለይ የጀበና ቡና የሚሸጡ ሰዎች ሲኒዎችን በጥንቃቄ እንዲያጥቡና እንዲቀቅሉ ይመክራል። ሆኖም ይህ መረጃ ሳይንሳዊ እውነታን ያዛባ ሲሆን በከፊል ብቻ እውነትነት ያለው መሆኑን MFC አረጋግጧል።

መረጃው ለምን በከፊል ብቻ እውነት ተባለ?
ጉበትን ከሚያጠቁ የቫይረስ አይነቶች መካከል በመረጃው ላይ የተጠቀሰው ሄፓታይተስ ኤ በንጽህና ጉድለት በበሽታው ከተጠቃ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን የቡና ሲኒዎች በደንብ ካልታጠቡ እና ካልተቀቀሉ ለሄፓታይተስ ኤ ስርጭት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም መረጃው ሄፓታይተስ ሲንም ጨምሮ መጥቀሱ ስህተት ነው።
በቲክቶክ ቪዲዮው ላይ እንደተጠቀሰው ሄፒታይተስ ሲ በቡና ሲኒ ንክኪ ወይም በምራቅ አይተላለፍም። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ቫይረሱ የሚተላለፈው ቀጥተኛ በሆነ የደም ንክኪ ብቻ ነው። ስለዚህ “ሲኒ ባለመታጠቡ ሄፒታይተስ ሲ ይስፋፋል” የሚለው ንግግር ከህክምና ሳይንስ ውጪ ነው። (የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እዚህ ይመልከቱ)
በሌላ በኩል መረጃውን ያሰራጨው ግለሰብ የትኛው የጤና ተቋም ወይም የመንግስት አካል ነው የመረጃው ምንጭ የሚለውን አልጠቀሰም። MFC መሰል የጤና ጉዳዮች በቀጥታ የሚመለከታቸው የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማህበራዊ ገጾች ላይ ባካሄደው ቅኝት ከሄፒታይተስ ኤ እና ሲ ስርጭት ጋር በተገናኘ የተሰጠ መግለጫ ወይም ማሳሰቢያ የለም።
አውድ
ስለ ሄፒታይተስ A እና C ማወቅ ያለብዎት እውነታዎች
ሄፒታይተስ ቫይረስ የጉበት በሽታ ሲሆን በተለያዩ የቫይረስ አይነቶች አማካኝነት ይከሰታል። በቲክቶክ ቪዲዮው ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አይነቶች የመተላለፊያ መንገዳቸው የተለያየ ነው።
ሄፒታይተስ ኤ (Hepatitis A) ፦ ይህ አይነቱ ሄፒታይተስ አጣዳፊ የጉበት ኢንፌክሽንን የሚያስከትል ሲሆን በአብዛኛው ከንጽህና ጉደለት የተነሳ ይከሰታል። የመተላለፊያ መንገዶቹም በቫይረሱ የተበከለ ምግብ ወይም ውሃ በመውሰድ እና በበሽታው የተያዘ ሰው ሽንት ቤት ተጠቅሞ እጁን በደንብ ሳይታጠብ ምግብ ካዘጋጀ ወይም ዕቃዎችን ከነካ ነው። ይሄንን የበሽታ አይነት ፥ ምግብ ከመመገብ በፊትና ከሽንት ቤት መልስ እጅን በሳሙና በመታጠብ ፣ የምግብ ማቅረቢያ ዕቃዎችን (ሲኒዎችን ጨምሮ) በንጹህ ውሃና ሳሙና በማጠብ እና ክትባት በመውሰድ መከላከል ይቻላል።
ሄፒታይተስ ሲ (Hepatitis C) ፦ ለተራዘመ የጉበት በሽታና ለጉበት ካንሰር ሊዳርግ የሚችል አደገኛ የቫይረስ አይነት ሲሆን የመተላለፊያ መንገዶቹም በቫይረሱ የተበከለ ደም ወደ ሰውነት ሲገባ ፣ ስለታም የሆኑ ቁሶችን (ምላጭ ወይም መርፌ) በጋራ በመጠቀም ፣ በወሊድ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ እና ንጽህናቸውን ያልጠበቁ የቀዶ ጥገና መሳሪያቸውን በመጠቀም ነው።
ሄፓታይተስ ሲ (Hepatitis C) በምራቅ፣ በትንፋሽ፣ በማቀፍ ወይም ምግብና መጠጥን በጋራ በመጠቀም አይተላለፍም።
መደምደሚያ
የጀበና ቡና ነጋዴዎች ሲኒዎችን በንጽህና ማጠባቸውና መቀቀላቸው ለጠቅላላ ጤና (በተለይም ሄፓታይተስ A እና መሰል በሽታዎች ለመከላከል) እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በሚገባ ግንዛቤ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሄፓታይተስ ሲ በሲኒ መጋራት እንደማይተላለፍም ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም MFC የተጠቀሰውን መረጃ ከፊል እውነት ሲል በይኖታል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ያልተረጋገጡ የጤና መረጃዎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡ እና ማንኛውንም የጤና ስጋት ሲሰሙ ከጤና ባለሙያ ወይም ከይፋዊ የጤና ተቋማት ገጾች ብቻ እንዲያረጋግጡ MFC ያሳስባል።
የግል ንጽህናዎን በመጠበቅ ከሄፒታይተስ ኤ ከአላስፈላጊ የደም ንክኪ ጥንቃቄ በማድረግ ደግሞ ከሄፒታይተስ ሲ ጤናዎትን ይጠብቁ።
