በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ላይ አንድ መንገደኛ በድንገት ህይወቱ እንዳለፈ የሚገልጽ መረጃ በሁለት የቲክቶክ ገጾች ተሰራጭቷል።
ብያኔ
ክስተቱ የተፈጠረው ከአንድ አመት በፊት ሲሆን ወቅታዊ አደጋ ተደርጎ በመቅረቡ MFC ሐሰት ሲል በይኖታል።
የማጣራት ስራ እና ግኝቶቹ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን ሲጓዝ የነበረ መንገደኛ በረራ ላይ ህይወቱ እንዳለፈ የሚገልጽ መረጃ ታህሳስ 15, 2018 ዓ/ም በሁለት የቲክቶክ ገጾች ላይ ተሰራጭቷል።
ከሰባ ሰባት ሺህ (77,000) እና ስድሳ ዘጠኝ ሺህ (69,000) በላይ ተከታይ ያላቸው የቲክቶክ ገጾች “አስደንጋጭ ሰበር ዜና” ከሚል የጽሑፍ መግለጫ ጋር “ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን በሚጓዝ አውሮፕላን አንድ መንገደኛ ህይወቱ አለፈ” የሚል ዜና አስተላልፈዋል። መረጃው ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ድረስ ብቻ በድምሩ ከሁለት መቶ ስድሳ አምስት ሺህ (265,000) በላይ ዕይታ አግኝቷል (እዚህ እና እዚህ ይመልከቱ)።

MultiFact Check (MFC) ተከስቷል የተባለውን አደጋ በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ ምንድነው? የሚል መነሻ በመያዝ የሀገር ውስጥ እና የውጪ የዜና ምንጮች እንዲሁም የአየር መንገዱ ገጾች ላይ ምርመራ አድርጓል።
በዚህም በቲክቶክ ልጥፎቹ ላይ ምስሉ ተቆርጦና ድምጹ ብቻ ተለይቶ የቀረበው መረጃ ባለቤት ማን እንደሆነ MFC ለይቷል። በመሆኑም የቲክቶክ ገጾቹ ድምጹን ብቻ ለይተው የወሰዱት ከNahoo Tv የቲክቶክ ገጽ ነው። ናሁ ቲቪ ከአንድ አመት በፊት ማለትም ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ/ም (November 19, 2024) በይፋዊ የቲክቶክ ገጹ ይሄንንኑ መረጃ አጋርቷል (እዚህ ይመለከቱ)።

በተጨማሪ በተመሳሳይ ቀን ዘ-ሐበሻ እና ጌጡ ተመስገን የተባሉ የዜና ገጾች የዋሽንግተን ዲሲ መዝናኛ መጽሔትን በምንጭነት በመጥቀስ ይሄንኑ መረጃ በፌስቡክ ገጾቻቸው አጋርተዋል (እዚህ እና እዚህ ይመልከቱ)።
አውድ
ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ/ም (November 15, 2024) ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ አየር መንገድ Airbus A350 አውሮፕላን በበረራ ቁጥር ET 500 ሲጓዙ የነበሩ አቶ ወንደሰን መኮንን የተባሉት ግለሰብ የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው ህይወታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል።
ለሟች የኃይማኖታዊ ሽኝት መርሃ ግብር ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ/ም (November 21, 2024) በቨርጂኒያ በሚገኘው ቅዱስ ራጉኤል እንደተካሄደ MFC አረጋግጧል (እዚህ ይመልከቱ) ። የቀብር ስነ ስርዓቱም በዕለቱ ተፈጽሟል።
መደምደሚያ
በሁለት የቲክቶክ ገጾች “ታህሳስ 15 ቀን 2018 አስደንጋጭ ዜና” በሚል በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሲጓዝ የነበረ መንገደኛ ህይወቱ እንዳለፈ በመግለጽ የቀረበው መረጃ የቆየ በመሆኑ MFC ሐሰት ሲል በይኖታል።
ማህበራዊ ሚዲያ ዜጎች መረጃዎችን የሚያገኙባቸው መድረኮች ከሆኑ ሰነባብቷል። በተለይም በቲክቶክ ዜናዎችን የሚያቀርቡ ግለሰቦች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከተ መጥቷል። በዚህም ጠቀሚታዎች ያሉት ይሄው መድረክ ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ፣ ጥላቻ ንግግር እና ሁከትን መስበኪያ መድረኮች ሲሆኑም ተመልክተናል።
