በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፦ በፌስቡክ ገጽ የተላለፈ በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ZU 23 የሚባል ታንክ በእጃቸው እንዳስገቡ ከሚገልጽ መረጃ ጋር አንድ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል።
ብያኔ፦ ከተጠቀሰው መረጃ ጋር የተለጠፈው ምስል ሀሰት ነው። ምስሉ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ የማያሳይ ሆን ተብሎ የቀረበ እና አሳሳች ነው።
የማጣራት ስራ እና ግኝቶቹ
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ZU 23 በሚል የሚታወቀውን ታንክ በእጃቸው እንዳስገቡ (እንደማረኩ) የሚገልጽ መረጃ ከአንድ ምስል ጋር በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት እየተሰራጨ ነው። በተለይም ከሃያ አራት ሺህ (24,000) በላይ ተከታዮች ያሉት “Amhara Focuse” የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ገጽ መስከረም 18 ቀን 2018 ዓ/ም ይሄንኑ መረጃ ምስሉን በማያያዝ ለጥፏል።
ልጥፉ ለብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ተደራሽ ሆኗል። ይህ ዘገባ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ መረጃውን ከአምስት ሺህ በላይ ግለሰቦች ግብረ መልስ ሲሰጡበት ሶስት መቶ ሰባ ሰባት (377) አስተያየቶችንም አስተናግዷል። (እዚህ ይመልከቱ)

በተጨማሪም ይሄንኑ መረጃ ከተመሳሳይ ምስል ጋር ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው የፌስቡክ ገጾች እና ግሩፖች አጋርተውታል። (እዚህ ፣ እዚህ እና እዚህ ይመልከቱ)
ከመረጃው ጋር ተያይዞ የቀረበው ምስል ላይ አጠራጣሪ ነገሮችን የተመለከተው MultiFact Check (MFC) ማጣራት አድርጓል። በዚህም ምስሉ በመረጃው ላይ እንደቀረበው አሁን በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ታጣቂ ኃይሎች የማረኩት ነው? የምስሉ ባለቤትስ ማነው? የሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮችን አጣርቷል።
MFC ባካሄደው የጉግል ሌንስ የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ ምስሉ ከዚህ በፊት ለቀረቡ የማህበራዊ ሚዲያ ዜናዎች በግብዓትነት ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበር በተለይም ከሶስት አመት በፊት ”እምዬ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ በሚጠቀም የፌስቡክ ገጽ ላይ መለጠፉን አረጋግጧል (እዚህ ይመልከቱ)።
በተጨማሪ ማጣራት ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፈው ጥር 18 ቀን 2014 ዓ/ም “ምስጋን ደስዬ” የሚል መጠሪያ ባለው የፌስቡክ ገጽ መሆኑ ታውቋል። ይሄው ግለሰብ በወቅቱ “ትህነግ” ሲል የጠራው የትግራይ ኃይል “የራያ ነዋሪዎች ላይ አስገዳች ውሳኔ አስተላልፏል ፡ ትዕዛዝ ከተሠጠ ልዩ ሀይላችን ፣ መከላከያ ሀይላችን፣ ሚኒሻችን፣ ፋኖው ፊት ለፊት በተጠንቀቅ ቆመናል።” በማለት ምስሉን ከሌላ ተጨማሪ አንድ ምስል ጋር አጋርቷል።
በምስሉ ላይ የሚታየው መልክዓ ምድር አሁን ላይ በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ታንክ በእጃቸው አስገብተዋል ከሚል መረጃ ጋር ከቀረበው ምስል ጋር የተለያየ መሆኑም በግልጽ ይታያል። (እዚህ ይመልከቱ)

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ታንክ እንደማረኩ በማስመሰል የቀረበው ምስል በግልጽ እንደሚታየው አሳሳች በሆነ መልኩ ለውጥ ተደርጎበታል። በተጨማሪም MFC የፎቶ ፎረንሲክ መገልገያ መሳሪያ ተጠቅሞ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ላይ ለውጥ እንደተደረገበት አረጋግጧል።

መደምደሚያ
በፌስቡክ ላይ ከተጋራ መረጃ ጋር ተያይዞ በቀረበው ምስል ላይ ባደረገው ማጣራት እነዚህን ውጤቶች አግኝቷል።
ሀ. ምስሉ በተለያዩ ወቅቶች ለቀረቡ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች በማሳያነት መቅረቡን፤
ለ. በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ZU 23 በመባል የሚታወቀውን ታንክ እንደማረኩ በቀረበው መረጃ ላይ የተያያዘው ምስል እንዲያሳስት ታስቦ ተቀናብሮ መቅረቡን (ይሄንንም የፎቶ ፎረንሲክ መገልገያ መሳሪያዎች አረጋግጠዋል)፤
ሐ. ትክክለኛው ምስል የተወሰደው እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለጠፈው ከሶስት ዓመት በፊት ጥር 18 ቀን 2014 ዓ/ም በፌደራል መንግስት እና ትግራይ ኃይሎች መካከል በነበረው ጦርነት ወቅት መሆኑን
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሰው የፌስቡክ ገጽ ካስራጨው መረጃ ጋር ተያይዞ የቀረበው ምስል ወቅታዊውን የአማራ ክልል ግጭት ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ZU 23 የሚባለውን ታንክ “በእጃቸው ሲያስገቡ” (ሲማርኩ) የሚያሳይ ባለመሆኑ MFC ሀሰተኛ ሲል በይኖታል።
ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እየጨመረና እየተራቀቀ መጥቷል። በተለይም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚወጡ የፎቶ እና ቪዲዮ መረጃዎች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረትና ጥንቃቄ ሊታዩ ይገባል። በዚህም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማንኛውንም መረጃ ከማሰራጨታቸው ወይም ግብረ መልስ ከመስጠታቸው በፊት የተላለፈው መረጃ ላይ ተገቢውን ማጣራት እንዲያደርጉ MFC ያሳስባል።
