ምስሉ ‘ሪፖርተር ጋዜጣ የምርጫ ውጤት የታወቀ’ ስለመሆኑ መዘገቡን አያሳይም

Thumbnail Image of a fact-checked article about reports of pre-known Ethiopian June 2026 Election outcome

በርኾቦት አያሌው

የተጠቀሰው መረጃ

በግንቦት 23/ 2019 ዓ.ም የወጣውን 31ኛ እትም ቁጥር 2722 የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ “ነው” በሚል በፌስቡክ ላይ አንድ ምስል ተጋርቷል። ምስሉን የለጠፈው የፌስቡክ ተጠቃሚም ጽሁፍ ያያያዘ ሲሆን ፤ “አንዳንድ ወረዳዎች ግን የምርጫ ኮሮጆውን በካርድ ሞልተው እንዳልጨረሱ ሰምተናል። ሪፖርተር ግን ብልጽግናን እየተፈታተናት ነው”ሲል ይነበባል። የሪፖርተር ጋዜጣን የፊት ገጽ ያሳያል ተብሎ የተጋራው ዜና ርዕስ “የምርጫ አሸናፊው የታዋቀ ስለሆነ ወደ ሚቀጥለው የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሠለጠነ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው” የሚል ዐቢይ ርዕስ የያዘ ነው።

ምስል 1፡ እየተዘዋወረ የሚገኘው የተቀናበረ ምስል

ብያኔ

ሀሰትMFC የልጥፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ባደረገው ጥረት ምስሉ የተቀነባበረ እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።


የማጣራት ሂደት እና ግኝቶች

MFC ምስሉን ይበልጥ ስልታዊ በሆኑ የፎረንሲክ ቴክኖሎጂዎችና የሰነድ ማነፃፀሪያ መንገዶች በመመርመር የሚከተሉትን ሦስት ቁልፍ ማስረጃዎች አግኝቷል፦

1. የይዘት እና የአርዕስት ማነፃፀር

በተሰራጨው የተዛባ ምስል እና በእውነተኛው የሪፖርተር ጋዜጣ እትም መካከል ግልጽ የሆነ የአርዕስት ልዩነት አለ። ተመሳሳይ ምስላዊ ገፅታ የሚያሳይ ቢሆንም በዋናው እትም የፊት ገፅ ላይ የወጣው ዜና አርዕስት ግን “የምርጫ ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ ወደ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሠለጠነ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው” ሲል ይነበባል። (የሪፖርተር ሙሉ ዘገባን እዚህ ያገኙታል።)

  • በተቀነባበረው ምስል ላይ ያለው፦ «የምርጫ አሸናፊው የታወቀ ስለሆነ ወደ ሚቀጥለው የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሠለጠነ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው»

  • በእውነተኛው የሪፖርተር ጋዜጣ እትም ላይ ያለው፦ «የምርጫ ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ ወደ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሠለጠነ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው»
ምስል 2፡ የተቀናበረው ምስል(ግራ) እና ኦሪጂናል የጋዜጣው የፊት ገጽ ምስል (ቀኝ) በንጽጽር

የሐሰተኛ መረጃ አቀናባሪዎቹ “ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ” የሚለውን ኃይለ-ቃል በመሰረዝ፣ በምትኩ “አሸናፊው የታወቀ ስለሆነ” የሚል ጥርጣሬና ውዥንብር የሚፈጥር ሐረግ ተክተውበታል። ከዚህም በተጨማሪ ከርዕሱ በታች ያለውን ክፍል ብናነብ ፤ “የተቀናበረው ምስል” ላይ ከተጻፈው ነገር የሚቃረን ሲሆን ይልቁንም የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ “የምርጫ ውጤትን በፀጋ ተቀብሎ ወደ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ መሸጋገር የሠለጠነ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው” ማለታቸውን ጽሁፉ ያስረዳል፡፡

ምስል 3፡ የዘገባውን ዝርዝር በቅርበት ለማሳየት (አጽንዖት የተጨመረ)
2. የፎረንሲክ ምስል ትንተና

MFC ምስሉን InVid Verification Plugin እና Fake Image Detector በተሰኙ የዲጂታል ፎረንሲክ መሣሪያዎች ውስጥ በማሳለፍ መርምሯል።

በምስል ማጉያ (Magnifier) እና የፒክሰል አሰላለፍ ትንተና (Pixel Grid Alignment) መሠረት፣ በዋናው አርዕስት ዙሪያ ያለው ነጭ የጀርባ ቀለም እና የፊደላቱ የጥራት ደረጃ እና የፊደል አይነት (ፎንት) በጋዜጣው ላይ ካሉ ሌሎች ጽሑፎች ጋር አይጣጣምም። የFake Image Detector ውጤት እንደሚያሳየውም ቢያንስ 50 % በኮምፒውተር የተቀናበረ ነው፡፡

ከአርዕስቱ ውጭ ያሉት ሌሎች የዜና አምዶች፣ የፎቶግራፍ መግለጫዎች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ (በምስሉ ላይ እንደቀረበው) ፎቶግራፍ ሳይለወጡ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል። ይህ የሚያሳየው አቀናባሪዎቹ አጠቃላይ ገጹን ሳይሆን ዋናውን ርዕስ ብቻ ነጥለው የዲጂታል ማሻሻያ ማድረጋቸውን ነው።

ምስል 4፡ ከ Fake Image Detector የተወሰደ ስክሪንሾት
3. የጊዜ ቅደም ተከተልና አመክንዮአዊ ግጭት

ጋዜጣው የታተመበት ቀን ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሆነ በጋዜጣው የፊት ገጽ ራስጌ ተጽፏል። ሆኖም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄደው ደግሞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ነው፡፡ ምርጫው ከመካሄዱ አንድ ቀን አስቀድሞ (ግንቦት 23 ቀን) የወጣ ጋዜጣ “የምርጫው አሸናፊ ታውቋል” ብሎ ሊዘግብ የሚችልበት ምንም ዓይነት አመክንዮአዊም ሆነ ሙያዊ አሠራር የለም። ይህም ምስሉ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ተብሎ የተፈበረከ መሆኑን ለማሳየት ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

አውድ

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቅን 2018 ዓ.ም እንድሚካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም አስታውቋል። ይህንን ተከትሎም በቅድመ ምርጫ ወቅት ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ፣ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ቅጥር ፣ ስልጠና እና ምደባ ፣ የምርጫ ክልል ወሰን ፣ የመራጮች ምዝገባ ፣ የሥርዓተ-ፆታ ማካተት ፣ የሚዲያ ተሳትፎ ፣ የሲቪክ እና የመራጮች ትምህርት ፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም ፣ የእጩ ምዝገባ ፣ የፖለቲካ ቅስቀሳ እና የመገናኛ ብዙሃን ናቸው።

የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተጠናቀቀ ሲሆን በአጠቃላይ ከ50 ሚልዮን በላይ መራጮች ተመዝግባዋል። ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ከሚገኙ 138 የምርጫ ክልሎች መካከል በስምንቱ እንዲሁም በትግራይ ክልል ደግሞ 38 የምርጫ ክልልሎች ምርጫ እንደማይደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በመሆኑም ይህ ልጥፍ የተጋራው በዚህ የምርጫ ሰሞን አውድ ውስጥ ነው፡፡

ማጠቃለያ

“የምርጫው ውጤት የታወቀ መሆኑን” ሪፖርተር ጋዜጣ መዘገቡን ለማሳየት የተጋራው የምስል ልጥፍ MFC ባደረገው የማጣራት ሂደት እና ግኝት መሰረት ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።

አንባቢዎቻችንም እንደዚህ አይነት ልጥፎችን በሚመለከቱበት ጊዜ ጉዳዩን ከምንጩ ወይም ከሚመለከታቸው አካላት በማረጋገጥ እና በማመሳከር እራሳቸውን ብሎም ሌሎችን ከሀሰተኛ መረጃ መከላከል ይችላሉ።

We at the MFC strive to verify misleading and false claims so that people get fact-based information and make an informed decision as well. In the process of our work, accuracy and transparency hold a central role. Therefore, if you see errors in our content, please write to us at info@multifactcheck.org so that our team will make corrections.

Share post on Social media

See related posts

ABOUT MFC

MultiFactCheck

(MFC) is an independent fact-checking organization which is launched to pin-point, track-down, scrutinize, investigate, interrogate, publish and distribute the factual accuracy of claims made by public figures. MFC’s project has geographical priorities. Our work mainly focuses on nations in the Horn of Africa and their diaspora community who reside abroad. We operates from various regions of Africa, Europe and North America. Through a multitude of professional proficiency, MFC deploys best practices of journalism, scholarship and expertise in order to flag, investigate and publish a fact.