በናኦል ጌታቸው
የተጠቀሰው መረጃ፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የሚታዩበት ቪዲዮ “ፋኖ ይችላል” ከሚል ድምፅ ጋር “በፋኖ የተማረኩ የመከላከያ አባላት” እንደሆኑ ተደርጎ አንድ ይዘት በቲክቶክ ላይ ተሰራጭቷል።
ብያኔ፦ ይሁን እንጂ ቪዲዮው ምስሉን ከሁለት ዓመት በፊት “በትግራይ ኃይሎች የተማረኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት” እንደሆኑ ከተሰራጩ ቪዲዮዎች ፤ እንዲሁም ድምፁን ደግሞ ከ6 ወራት በፊት “በፋኖ የተማረኩ መከላከያ ሰራዊት አባላት” ተደርገው የተሰራጩ ቪዲዮዎች የተቀናበረ በመሆኑ ሐሰት ሲል MFC በይኖታል።
Ethio Viral የተባለ እና ከ30,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ አካውንት “መከላከያ መጨረሻው በቃ እንደዚህ ይሁን” የሚል ፅሁፍ የተለጠፈበት ቪዲዮ በመጋቢት 21/2016 ዓ.ም. አጋርቷል። “ፋኖ ፋኖ .. ሁሌም ያሸንፋል…” የሚል ድምፅ (Voice Over) ያለውና “የተማረኩ” ወታደሮች የሚታዩበት ቪዲዮ ከ120,000 በላይ እይታ ሲያገኝ ከ1,500 ጊዜ በላይም ተጋርቷል።
ይሁን እንጂ MFC የተጠቀሰውን ቪዲዮ ትክክለኝነት ያጣራ ሲሆን ቪዲዮው የቆየ እና ከአማራ ክልል ግጭት እና ከ”ፋኖ ትግል” ጋር የሚያያዝ አለመሆኑን አረጋግጧል።
MFC ከቪዲዮው ላይ የተወሰዱ ስክሪንሹቶችን በጎግል የምስል ማፋለጊያ መሳሪያ ያጣራ ሲሆን ቪዲዮው ከሁለት ዓመት በፊት በጥቅምት 8/2014 ዓ.ም. በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች “በትግራይ ኃይሎች የተማረኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት” እንደሆኑ ከተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ የተወሰዱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። (ለአብነትም ይህንን ፣ ይህንን እና ይህንን መስፈንጠሪያ ይመልከቱ)
ከዚህም በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሰው የቲክቶክ አካውንት ቆየት ያለውንና ከወቅቱ የአማራ ክልል ግጭት ጋር ግንኙነት የሌለውን የቪዲዮ ምስል በመጠቀም ድምፁን ደግሞ ከሌሎች ቪዲዮዎች ላይ መውሰዱን ለማወቅ ተችሏል። ይህም ድምፁ ከስድስት ወራት በፊት “በፋኖ የተማረኩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት” በሚል ከተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ የተወሰደ ነው። (ለአብነትም ይህንን እና ይህንን መስፈንጠሪያ ይመልከቱ።)
በመሆኑም ቪዲዮው በቲክቶክ አካውንቱ አማካይነት በተሰራጨው መልኩ አንድ ወጥ ይዘት እና ወቅታዊውን የአማራ ክልል ግጭት የሚያሳይ ሳይሆን ፤ ከተለያዩ ይዘቶች የቆየ ምስልና ድምፅ የተቀጠለ ይዘት በመሆኑ ፤ በተጨማሪም ከሁለት ዓመታት በላይ የቆየና ከፋኖና የኢትዮጵያ መንግስት ግጭት ጋር ተያያዥነት የሌለው የቪዲዮ ምስል በመሆኑ MFC ሐሰት ሲል በይኖታል።
በተመሳሳይ መንገድ Dirbabaaa Darabaa የተባለ እና ከ14,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ አካውንት አንድን ቪዲዮ ድምፁን ከሌላ ቪዲዮ በመውሰድና በማቀናበር ያጋራ ሲሆን ይህም ከ400,000 በላይ እይታ አግኝቷል። ከዚም በተጨማሪ እንደፌስቡክ ባሉ ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎችም መጋራቱን ተመልክተናል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምስልን ከሌላ ቪዲዮ እንዲሁም ድምፁን ደግሞ ከሌላ በመገጣጠም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ማደናገር እና ማሳሳት እየተለመደ በመምጣቱ ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥንቃቄ በማድረግ ከተመሳሳይ አሳሳች ይዘቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ እናሳስባለን።
ድምፃቸውና ምስላቸው ከተለያዩ ይዘቶች የተቀጠሉና ሆን ተብለው ለማሳሳት የሚሰራጩ መረጃዎችን ለመለየት የሚከተሉትን መንገዶች ይጠቀሙ።
- ይዘቱን በሚገባ በማጤን የሚሰማው ድምፅ እና ምስሉ ላይ የሚታዩት ሰዎች የሚናገሩት በትክክል የሚገጥም መሆኑን መመልከት
- ይዘቱን የተመለከቱት በፊስቡክ ፣ በዩቲዩብ ወይም በX ከሆነ ከቪዲዮው ላይ በሚገባ ከሚታየው ክፍል ስክሪንሾት በመውሰድ በምስል ማፋለጊያ መሳሪያዎች (እንደ Google Reverse Image Seach ፣ Tineye እና ሌሎች) መመርመር። ይህም ተመሳሳይ ቪዲዮ ከዚህ ቀድም በሌላ ድምፅ (ምናልባትም ትክክለኛው) በኢንተርኔት ላይ ተሰራጭቶ እንደሆነ ለማግኘት ይረዳዎታል።
- ይዘቱን የተመለከቱት በቲክቶክ ከሆነ ደግሞ ከታች በምስሉ ላይ ቀስቱ የተመላከተበትን ቦታ በመንካት ተመሳሳዩን ድምፅ ከዚህ ቀደም ሌሎች ተጠቅመውበት ከሆነ ይጠቁምዎታል (ከታች ያለውን ስክሪንሾት ይመልከቱ)።