በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፡ ኢቢሲ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በ2016 የችግኝ መርሃ ግብር እያንዳንዷ ችግኝ ያረፈችበትን ቦታ መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉን ዘግቧል
ብያኔ፡ የቀረበው ዜና አሳሳች ሲሆን ችግኝ የተተከለባቸውን አጠቃላይ ስፍራዎችን መለየት የሚያስችል በካርታ የማካለል ስራ ብቻ ነው የተደረገው
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ነሃሴ 17 ቀን 2016 በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በኩል “እያንዳንዷ ችግኝ ያረፈችበትን ቦታ መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉ ተገለጸ” የሚል ዜና አጋርቷል።
መረጃው ይህ ጽሑፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ 3300 (ሶስት ሺህ ሶስት መቶ) ግብረ መልስ ሲያገኝ 808 (ስምንት መቶ ስምንት) አስተያየት ተሰጥቶበታል። እንዲሁም ለሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን 124 (አንድ መቶ ሃያ አራት) ጊዜ ተጋርቷል።
MFC ባካሄደው ዳሰሳ ከ10 በላይ የዜና ማሰራጫ የፌስቡክ ገጾች ሙሉ ዜናውን በመውሰድ ለተከታዮቻቸው ተደራሽ እንዲሆን ለጥፈዋል። የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም በዜናው ልጥፍ አስተያየት መስጫ ስር መረጃው እንዲጣራ ጠይቀዋል።
በመሆኑም MFC በዚህ አመት በተከናወነው የ”አረንጓዴ አሻራ” ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር እያንዳንዷ ችግኝ ያረፈችበትን ቦታ መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ተደርጓል? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ የማጣራት ስራ አድርጓል።
ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ኃላፊ ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያ ለMFC ሰጥተዋል።
“የዜናው ርዕስ የቀረበበት መንገድ ስህተት ነው” ያሉት ኃላፊው “በዜናው መጨረሻ ላይ 8454 (ስምንት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ አራት) ቦታዎች በካርታ መለየቱን ይገልጻል ፥ ይህም ማለት ለምሳሌ መስቀል አደባባይ አካባቢ የተተከለ ሳይት ካለ ሙሉ ሳይቱ Map ተደርጓል ማለት ነው” ብለዋል።
“ቴክኒካል በሆነ መንገድ የእያንዳንዱን ችግኝ ሎንግቲውድ እና ላቲቲውድ መዝግቦ Map ማድረግ የሚቻል ቢሆንም እንደዛ አልተደረገም ከፍተኛ ወጪም ይጠይቃል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“በዜናው ላይ ለማለት የተፈለገው የተተከለበት ቦታ ከዚህ በፊት እንደነበረው እዚህ ቦታ ተተክሏል ብቻ ሳይሆን ጆኦ ሪፈራል ተደርጓል ማለትም የት የት እንደተተከሉ ካርታ ላይ ማወቅ ይቻላል’ በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ አረንጓዴ አሻራ በሚል ንቅናቄ የችግኝ ተከላ የጀመረው በ 2011 ዓ/ም ሲሆን የ 2016 ዓ/ምን ሳይጨምር በድምሩ 22 ቢሊየን 500 ሚሊየን ችግኝ እንደተተከለ ይገልጻል። መንግስት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በ 2011 ከተተከሉ ችግኞች ከ83 በመቶ በላይ እንዲሁም በ2012 ከተተከሉት 79 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ቢገልጽም ገለልተኛ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ተቋማት አይስማሙ።
ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ያደረገው International Institute for Environment and Development (IIED) ባልደረባ የሆኑት ጄምስ ሜይርስ “በመንግስት የቀረቡት አሃዞች አስተማማኝ አይደሉም ፥ ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ስላለው ሁኔታ መከታተል የሚያስችል ዘዴ መዘጋጀት አለበት” ብለዋል (ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች ከBBC አማርኛ እዚህ ይመልከቱ)።