ፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፡ ጎንደር ላይ ፋኖን የሚቃወም ሰልፍ እንደተደረ የሚገልጽ ጽሁፍ ከቪዲዮ መረጃ ጋር በ “X” ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርቷል።
ብያኔ፡ የተጋራው የቪዲዮ መረጃ በራያ አላማጣ የህወሃት ታጣቂዎችን በመቃወም የተደረገ ሰልፍን የሚያሳይ ነው።
ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ/ም Habitsh Gurmu የሚል ስያሜ ያለው የX ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ አካውንት “ፋኖን የሚቃወም ሰልፍ በጎንደር” የሚል መረጃ ከቪዲዮ ማስረጃ ጋር አጋርቷል።
የ 22 ሴኮንድ ርዝመት ባለው ቪዲዮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የተለያዩ መፈክሮች ይዘው ይታያሉ። በዚሁ ቪዲዮ ላይም አንድ ግለሰብ “የታጠቁ ኃይሎች ፥ ትምህርት ቤት ላይ የመሸጉ ኃይሎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ለቀው ይውጡልን” የሚል መፈክር ሲያሰማ ህዝቡም ሲያስተጋባ ይደመጣል።
MFC የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት የGoogle Reverse Image መረጃ ማጣሪያን የተጠቀመ ሲሆን ቪዲዮው የተቀረጸው ሰኔ 2 ፣ 2016 ዓ/ም ቢሆንም በጎንደር ፋኖን በመቃወም የተደረገ ሰልፍ አለመሆኑን አረጋግጧል።
ቪዲዮው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በሕወሓት እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በሕዝባዊ ሰልፍ አውግዘዋል” ከሚል ርዕስ ጋር ነው።
በተጨማሪም ከዚህ በታች ባለው ምስል እንደሚታየው የሰልፉ ተሳታፊዎች በእጅ የያዟቸው መፈክሮች ሰልፉ ህወሃትን ለመቃወም የተካሄደ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
በመሆኑም የፋኖ ሃይሎችን የሚቃወም ሰልፍ በጎንደር ከተማ ተካሄደ በሚል ከቪዲዮ ማስረጃ ጋር የቀረበውን ልጥፍ ሀሰት መሆኑን MFC አረጋግጧል።
ሰላማዊ ሰልፉ ከመደረጉ አስቀድሞ ግንቦት ወር ላይ የህወሃት ኃይሎች በአላማጣ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መስፈራቸው ተዘግቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ኃይሎች ከሰፈሩባቸው የአላማጣ ከተማ አቅራቢያ ስፍራዎች ለቀው እንዲወጡ አስተዳደራቸው መወሰኑን ይፋ አድርገው ነበር።
የትግራይ እና የአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት የራያ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ወራት በነበሩ አለመረጋጋቶች ከ50 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት መረጃ ያሳያል።