በናኦል ጌታቸው
የተጠቀሰው መረጃ ፦ አንድ ቪዲዮ በዕለቱ የነበረን “የፋኖ ኦፕሬሽን” እንደሚያሳይ ተደርጎ በX ማህበራዊ የትስስር መድረክ ተሰራጭቷል።
ብያኔ፦ የተጠቀሰው መረጃ ከ5 ወራት በፊት በአፍጋኒስታን የነበረን ሁኔታ የሚያሳይ እንጂ የአዲስ አበባን ክስተት የሚያሳይ ባለመሆኑ ሐሰት ነው።
Neba የሚል ስም ያለውና ከ4,400 በላይ ተከታዮች ያሉት የX አካውንት በሚያዝያ 4/2016 ዓ.ም. ቪዲዮ አጋርቷል። ይህ “የዛሬው ቦሌ ላይ የነበረው የ#Fano Operation ሙሉ ቪዲዮ” ከሚል ፅሁፍ ጋር የተጋራው ቪዲዮ ይህ የሀቅ ማጣራት ፅሁፍ እስከሚታተም ድረስ ብቻ ከ37,000 በላይ ዕይታ አግኝቷል።
ይሁን እንጂ MFC ባደረገው ማጣራት ቪዲዮው በዕለቱ የነበረውን የቦሌ አዲስ አበባ ሁኔታ አያሳይም።
ምስል፤ ከላይ በተጠቀሰው የX አካውንት ከተጋራው ይዘት በሚያዝያ 9/2016 የተወሰደ ስክሪንሾት
ከቪዲዮው ላይ ስክሪንሾቶችን በመውሰድ በጎግል የምስል ማፋለጊያ መሳሪያ በተደረገው ማጣራት ፣ ቪዲዮው የሚያሳየው አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ያለው የታሊባን ታጣቂ ወታደሮች በባለጎማ መንሸራተቻ ጫማ ሆነው የዋና ከተማዋን የካቡልን ጎዳናዎች ሲቃኙ ራሳቸውን የቀረፁበትን የቪዲዮ ቅጂ ነው።
ይህም ከአምስት ወራት በፊት የሆነ ሲሆን ዘ ቴሌግራፍ ፣ ዘ ኢኮኖሚስት ፣ እና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት በኩል በተሰራ ዘገባ የተሰራጨ ነው።
ምስሎች: ከ The Telegraph እና The Economist የሚዲያ አውታር የዩቲዩብ ቻናሎች በሚያዝያ 9/2016 ዓ.ም. የተወሰዱ ስክሪንሾቶች
በተጨማሪም የተጠቀሰውን መረጃ ያሰራጨው አካውንት ከአፍጋኒስታን በተወሰደው ቪዲዮ ላይ ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ በነበረ “የታላቅ ሩጫ” ላይ የተሰማ “እየመጡ ነው እየመጡ ነው” የሚል የህብረት “ዜማ/ሆታ”ን ድምፅ በቅንብር አካትቶበታል።
በመሆኑም MFC ባደረገው ማጣራት የተጠቀሰው መረጃ ከ5 ወራት በፊት በአፍጋኒስታን የነበረን ሁኔታ የሚያሳይ እንጂ የአዲስ አበባን ክስተት የሚያሳይ ባለመሆኑ ሐሰት ሲል በይኖታል።
አውድ
ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም. በመሐል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ፖሊስ የፋኖ አባላት ናቸው ካላቸው ግለሰቦች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጎ ሁለቱን መግደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።
የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችም እንደዘገቡት በቦሌ ክፍለ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የፋኖ “አመራር” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን ፤ በዚህም ከታጣቂዎቹም ከፖሊስም ወገን የሞቱ መኖራቸው ተዘግቧል።
ይህም ክስተት በሁለቱ ወገን በተለያየ መልኩ ተዘግቧል። ይህም በመንግስት በኩል “በጽንፈኛው ኃይል አመራርና አባላት ላይ እርምጃ” እንደተወሰደ ተደርጎ ሲዘገብ ፤ በታጣቂዎቹ በኩል ደግሞ “ፋኖ በአዲስ አበባ ያከናወነው የወታደራዊ ኦፕሬሽን” ተደርጎ በየሚዲየው ተሰራጭቷል።
ከላይ የተጠቀሰው መረጃም በዚህ አውድ የተሰራጨ ይዘት ነው።