በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፡ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን “የአማራ ህዝብ ተነስቷል። የአማራ አርሶ አደር ሆ ብሎ ወጥቷል” የሚል መረጃ ከአንድ ምስል ጋር ከ224ሺ በላይ ተከታዮች ባለው የፌስቡክ ገጽ ላይ አጋርቷል።
ብያኔ፡ ምስሉ የቆየ ሲሆን አሁናዊ በሆነው የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ላይ ለመሳተፍ የወጣ አርሶ አደርን የሚያሳይ አይደለም።
የቀድሞው ኢሳት ቴሌቭዥን ጣብያ ጋዜጠኛ እና በአሁን ሰዓት Anchor Media የተባለ የዩቲውብ ሚዲያ አዘጋጅ መሳይ መኮንን ከ224ሺ በላይ ተከታዮች ባለው የፌስቡክ ገጹ በኩል ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ/ም “ይናገራል ፎቶ” የሚል ጽሑፍ ከአንድ ምስል ጋር አጋርቷል።
ጋዜጠኛው በዚሁ ልጥፍ ላይ “ጃውሳ እያልክ አትጃጃል። ፎጤ ብለህም አትለፋደድ። የአማራ ህዝብ ተነስቷል። የአማራ አርሶ አደር ሆ ብሎ ወጥቷል” በማለት ይገልጻል።
መረጃው ይህ ጽሑፍ ለንባብ እስከበቃበት ድረስ ከሁለት ሺ ስድስት መቶ በላይ ግብረ መልስ አግኝቷል። 89 ጊዜም ለሌሎች የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን ተጋርቷል።
በአማራ ክልል በፌደራል መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና የጦር መሳሪያ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለአንድ አመት የዘለቀ ግጭት እንዳለ ይታወቃል (እዚህ ያንብቡ)።
ከጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የፌስቡክ ልጥፍ ጋር ተያይዞ የቀረበው ምስል አሁን ላይ “የአማራ አርሶ አደር ሆ ብሎ…” መውጣቱን ያሳያል? በሚለው አውድ ዙሪያ MFC የማጣራት ስራ ሰርቷል። በዚህም ከጋዜጠኛው ሃሳብ ጋር ተያይዞ የቀረበው ምስል በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት የማያሳይ አሳሳች ምስል መሆኑ ተረጋግጧል።
ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ ጥቅም ላይ የዋለው ከ7 አመታት በፊት የካቲት 30, 2009 ዓ/ም (March 9, 2017) “ወጀራት.com” በተባለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ነው። በተጨማሪም የፌስቡክ ገጹ በድጋሚ ምስሉን በመጋቢት 3, 2009 ዓ/ም (March 12, 2017) “የወጀራት ሽማግሌዎች ጀግኖች ፣ እምቢ ባዮች እና ልባሞች” የሚል ይዘት ካለው ግጥም ጋር አጋርቶታል (ይሄንን እና ይሄንን ይመልከቱ)።
በተጨማሪም የጉግል ምስል ማሰሻ (Google Lens) ምስሉ በተለያየ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ ለተሰራጩ መረጃዎች አባሪ ሆኖ ጥቅም ላይ እንደዋለ ያሳያል።
በመሆኑም “የአማራ ህዝብ ተነስቷል ፥ የአማራ አርሶ አደር ሆ ብሎ ወጥቷል” በሚል በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የተጋራው ምስል የቆየ እና በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ተሳታፊ ለመሆን የወጣ ህዝብን የሚያሳይ አይደለም።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በተለይም ደግሞ ጋዜጠኞች በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ የሚያጋሯቸውን የጽሁፍ ፣ ምስል እንዲሁም ቪዲዮ መረጃዎች ከማሰራጨታቸው በፊት አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እንዲያከናውኑ እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቀነስ የበኩላቸውን እንዲወጡ MFC ያሳስባል።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት እንዲፈርስ እና በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተካቶ እንዲደራጅ የፌደራል መንግስት ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ጦርነት የተቀሰቀሰው።
ከሀምሌ 2015 ጀምሮ የታወጀው እና በክልሉ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ በመላው ሀገሪቱ ተፈጸሚ እንዲሆን ለ10 ወራት ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባሳለፍነው ግንቦት ወር የተፈጻሚነት ጊዜው አብቅቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 የሀገሪቱን ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በተለምዶ “ፋኖ” ተብሎ በሚታወቁ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው የትጥቅ ግጭት በክልሉ ሁሉም ዞኖች መስፋፋቱን ይገልጻል። ይሄው በትጥቅ የታገዘ ግጭትም በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ጠቁሟል (ሙሉ ሪፖርቱን ይመልከቱ)።