የተጠቀሰው መረጃ፦ አንድ የX አካውንት “በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት እየተካሄደ ነው” የሚል ትርጉም ካለው የእንግሊዘኛ ፅሁፍ ጋር በማያያዝ አንድ “ዘግናኝ” ይዘት ያለው ምስል ለጥፏል።
በያኑ፦ ምስሉ (አሁን) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለን “የዘር ማጥፋት” የሚያሳይ ሳይሆን ከአምስት አመት በፊት በሐሰተኛ መረጃ ምክንያት የደቦ ፍርድ ጥቃት ሰለባ የሆነን ግለሰብ ዘገናኝ ምስል የሚያሳይ በመሆኑ የተጠቀሰው መረጃ ሀሰት ነው።
Zoom Afrika, የሚል ስም ያለው እና ከ274,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የX አካውንት “በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት እየተካሄደ ነው” የሚል ትርጉም ካለው የእንግሊዘኛ ፅሁፍ ጋር በማያያዝ ፎቶ አጋርቷል። ይህም ትዊት ይህ ፅሑፍ እስከሚታተም ድረስ ከ102,000 በላይ እይታዎች እና ከ800 በላይ ገብረ መልስ ሲያገኝ ከ480 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።
ይሁን እንጂ አካውንቱ ፅሁፉን እንዲድግፍለት ያያዘው ፎቶ የቆየ እና በሌላ አውድ ውስጥ የተፈጠረን ክስተት የሚያሳይ ነው።
MFC የጎግል ምስል ማፋለጊያ መሳሪያን በመጠቀም ምስሉን ለማጣራት ባደረገው ጥረት የመጀመሪያው የምስሉ ምንጭ ወይም ባለቤት ማን እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም። ይሁን እንጂ መሳሪያው ይህ ምስል ከአምስት አመታት በፊት የተሰራጩትን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት መሰራጨቱን ያሳያል።
በመሆኑም ይህ ዘግናኝና አሳዛኝ ክስተትን የሚያሳየው ምስል ከአምስት አመታት በፊት በነሃሴ 6/2010 አ.ም በሻሸመኔ ከተማ በወቀቱ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዳይሬክተር የነበረውን አቶ ጃዋር መሕመድን እና ለሌሎች የቡድኑ አባላት አቀባበል ለማድረግ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ከተከሰተ “የደቦ ፍርድ” የተወሰደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በእለቱም “ቦንብ ይዟል” በሚል ሐሰተኛ መረጃ ምክንያት በአንድ ግለሰብ ላይ በደቦ አሰቃቂ ግድያ በአደባባይ የተፈፀመ ሲሆን ምስሉ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በስፋት ተዘዋውሯል። (ለአብነትም ይህንን ፣ ይህንን እና ይህንን ማስፈንጠሪያ ይመልከቱ።)
በመሆኑም ምስሉ በX አካውንቱ እንደተጠቀሰው (አሁን) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለን የዘር ማጥፋት የሚያሳይ ሳይሆን ከአምስት አመት ከ8 ወራት በፊት በሻሸመኔ ከተማ በሐሰተኛ መረጃ ምክንያት የደቦ ፍርድ ጥቃት ሰለባ የሆነን ግለሰብ ዘገናኝ ምስል የሚያሳይ በመሆኑ የተጠቀሰው መረጃ ሀሰት ነው።