በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፡ በጎፋ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር 300 ደርሷል ከሚል መረጃ ጋር አንድ ቪዲዮ በቲክቶክ ተሰራጭቷል
ብያኔ፡ መረጃው በተሰራጨበት ወቅት የሟቾች ቁጥር 300 መድረሱ አልተረጋገጠም ከመረጃው ጋርም የተያያዘው ቪዲዮ እ.አ.አ በ 2022 በህንድ ግዛት የተከሰተ የመሬት መንሸራተት የሚያሳይ ነው።
ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ/ም ከ99ሺ በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ አካውንት “በጎፋ ዞን መሬት መንሸራተት የሞቱት 300 ሰው ደረሰ” ከሚል ጽሑፍ ጋር የመሬት መንሸራተት ሲከሰት የሚያሳይ ቪዲዮ አጋርቷል።
ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ቪዲዮው ከ 2 ሚሊየን 500ሺ በላይ ሰው የተመለከተው ሲሆን ከ186ሺ በላይ ግብረ መልስ እና 4664 አስተያየት ሲያገኝ ከ118ሺ ጊዜ በላይ ተጋርቷል።
ሆኖም ምንም እንኳን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተ ቢሆንም ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር 257 ሲሆን ከመረጃው ጋር ተያይዞ የቀረበው ቪዲዮ ሀሰተኛ እና በጎፋ ያለውን አደጋ የሚያሳይ አለመሆኑን አረጋግጠናል።
MFC የተለያዩ የሀቅ ማጣሪያ መንገዶችን በመጠቀም አጣርቶ የቪዲዮውን ትክክለኛ መረጃ አግኝቷል። በዚህም ቪዲዮው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው CNN News 18 በተባለው ከ7 ሚሊየን 800ሺ በላይ ሰብስክራይበር ባለው የህንድ የዜና አውታር ይፋዊ የዩቲውብ ገጽ ላይ ነው። (እዚህ ይመልከቱ)
በዚህም ቪዲዮው እ.ኤ.አ በ2022 በሰሜናዊ ምስራቅ ህንድ በምትገኘው ሜጋሊያ ግዛት የደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋን የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ከሚገልጽ መረጃ ጋር የተጋራውን ቪዲዮ MFC ሀሰት በማለት በይኖታል።
ሐምሌ 14 2016 ዓ/ም በክልሉ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት በማግስቱ ሐምሌ 15 2016 ዓ/ም በተሰባሰቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የመሬት መንሸራተት አደጋ ደርሶባቸዋል።
ይህ ጽሑፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ250 በላይ ሰዎች ህይወት በአደጋው ተቀጥፏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ኦቻ (OCHA) በአደጋው የሞቱ ዜጎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ጠቁሟል። (እዚህ ይመልከቱ)
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚመለከቷቸው መረጃዎች ላይ ግበረመልስ ከመስጠታቸው እና ከማጋራታቸው አስቀድመው የመረጃውን እና ከመረጃው ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የምስል እና ቪዲዮ ማስረጃዎችን እንዲመረምሩ እንዲሁም ትክክለኛነታቸውን እንዲያረጋግጡ MFC ያበረታታል።