በፋሲል አረጋይ
የተጠቀሰው መረጃ፡ በኦሮሚያ መቂ ከተማ ጥቃት መፈጸሙን አሽከርካሪዎች መገደላቸውን እና በተሽከርካሪ ላይ ጉዳይ እንደደረሰ የሚገልጽ መረጃ ከምስል ማስረጃዎች ጋር በቴሌግራም ተሰራጭቷል
ብያኔ፡ ሐሰት፦ ምስሎቹ በመቂ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት የደረሰ ጉዳትን የሚያሳይ አይደለም
መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ/ም “Ayu zehabesha official” የሚል ስያሜ የሚጠቀም 222,591 (ሃያ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ዘጠና አንድ) ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻናል “በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት የ4 አሽከርካሪዎች ህይወት ሲያልፍ ከ30 በላይ ተሽከርካሪዎች ጉዳት አስተናግደዋል” የሚል መረጃ ከሁለት ምስሎች ጋር አጋርቷል።
ልጥፉ ይህ ጽሑፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ብቻ 37,000 (ሰላሳ ሰባት ሺህ) የቴሌግራም ተጠቃሚዎች የተመለከቱት ሲሆን 200 (ሁለት መቶ) ግብረ መልስ አግኝቷል።
መረጃው ከቴሌግራም በተጨማሪ በሌሎች የዜና ማስተላለፊያ ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የተሰራጨ ሲሆን MFC ባካሄደው ዳሰሳ ከ 33 በላይ የፌስቡክ ገጾች መረጃውን ከተመሳሳይ ምስል ጋር ለተከታዮቻቸው አጋርተዋል። (ለምሳሌ ይሄንን ፣ ይሄንን እና ይሄንን ይመልከቱ)
በመሆኑም MFC በመረጃው ትክክለኛነት እና ከመረጃው ጋር ተያይዘው በቀረቡት ሁለት ምስሎች ትክክለኛነት ላይ ማጣራት አድርጓል።
በዚህም ከመረጃው ጋር ተያይዘው የቀረቡት ሁለት ምስሎች በመቂ ከተማ የተፈጸመ ጥቃትን የሚያሳዩ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።
የመጀመሪያው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ የተለቀቀው ህዳር 12 ፣ 2012 ዓ/ም “Voss” በተባለ እና 210ሺ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጽ ሲሆን ምስሉ በአዋሽ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች ሲቃጠሉ የሚያሳይ እንደሆነም ይገልጻል (እዚህ ይመልከቱ)
በተመሳሳይ በመቂ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት የደረሰ በሚል የቀረበው ሁለተኛ ምስል በአምቦ ከተማ ከስኳር እጥረት ጋር በተያያዘ ጥቅምት 16 ፣ 2010 ዓ/ም በተፈጠረ ግጭት የደረሰውን ውድመት የሚያሳይ እንደሆነ MFC አረጋግጧል። (ይሄንን እና ይሄንን ይመልከቱ)
በመሆኑም “Ayu zehabesha official” የሚል ስያሜ የሚጠቀም የቴሌግራም ቻናል ካስተላለፈው መረጃ ጋር የቀረቡት ሁለት ምስሎች በመቂ ከተማ የተፈጸመ ጥቃትን የማያሳዩ በመሆኑ MFC ሐሰት በማለት በይኖታል።
በመቂ ከተማ በመረጃው ላይ እንደተጠቀሰው ጥቃት ተፈጽሞ ጉዳት ደርሷል? የሚለውን በተመለከተ MFC በቀጥታ ጉዳዩን ማረጋግጥ አልቻለም።
ነገር ግን አሻም ቲቪ አርብ መስከረም 3 ፣ 2017 ዓ/ም በይፋዊ የዩቲውብ ገጹ ላይ በለጠፈው ዕለታዊ ዜናው በምስራቅ ሸዋ መቂ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ የአራት አሽከርካሪዎች ህይወት ማለፉንና ከ 30 በላይ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ከጥቃቱ ያመለጡ እና የሟች ቤተሰቦች ነግረውኛል በማለት ዘግቧል። (ይሄንን ይመልከቱ)
ሆኖም የከተማዋን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ ከመጠቀም ውጪ “Ayu Zehabesha Official” የተባለው የቴሌግራም ቻናል የተጠቀመውን ወይም ሌላ ጉዳቱ ያሳያል በሚል የቀረበ የምስል ወይም የቪዲዮ ማስረጃ የለም።