በናኦል ጌታቸው
የተጠቀሰው መረጃ፦ “አቶ ታዲዮስ ታንቱ ከእስር ተፈትተዋል” የሚሉ መረጃዎች በፌስቡክ እና በትዊተር ላይ እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ብያኔ፦ መረጃዎቹ ሐሰት ናቸው።
“አቶ ታዲዮስ ታንቱ ከእስር ተፈትተዋል” የሚሉ መረጃዎች በፌስቡክ ( ለአብነት ይህንን ፣ ይህንን ፣ ይህንንናይህንን መስፈንጠሪያዎች ተጠቅመው ይመልከቱ) እና በትዊተር ላይ ( ለአብነትይህንንናይህንን መስፈንጠሪያዎች ተጠቅመው ይመልከቱ) በግንቦት 30/ 2016 አ.ም. ሲሰራጩ ውለዋል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ አካውንቶች የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው።
መረጃዎቹ ሲሰራጩም ከአንድ ፎቶግራፍ ጋር መዘዋወራቸውን ለመመልከት ተችሏል። MFC ፎቶውን በGoogle Reverse Image ያጣራ ሲሆን ምስሉ ከሶስት አመት በፊት አቶ ታዲዮስ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ በፌስቡክ ላይ የ“እንኳን አደረስዎ” መልእክት ሲያሰተላልፉ የተሰራጨ ምስል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል (ለአብነት ይህንን ፣ ይህንን ፣ ይህንንና ይህንን መስፈንጠሪያዎች ተጠቅመው ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ ፎቶው ለመጀመሪያ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመታየቱን እንጂ በትክክል መቼ እንደተነሳ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በወቅቱ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በወንጀል ተጠርጥረው ከሚያዝያ 27 ቀን 2013 አንስቶ ለሰላሣ ቀናት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ በአራት ሺህ ብር ዋስትና ነበር የተለቀቁት።
ከዚህም በተጨማሪ MFC የአቶ ታዲዮስ ታንቱ ባለቤት የሆኑትን ወ/ሮ ጸጋ ሞገስን በስልክ ያነጋገረ ሲሆን መረጃው ሐሰተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ መግለጫ ያወጣ ሲሆን “አቶ ታዲዮስ ታንቱ በዛሬው ዕለት ከእስር ተፈቱ ተብሎ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሠራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” በማለት ገልጿል።
በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት መረጃዎች መሰረት MFC አቶ ታዲዮስ ታንቱ ከእስር ተፈትተዋል የሚለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
አውድ
አቶ ታዲዮስ ታንቱ በኢትዮጵያ የሚዲያና የፖለቲካ መድረክ የታወቁ ሰው ሲሆኑ ለረጅም ጊዜ አነጋጋሪ የታሪክ ሀሳቦችን በተለያዩ መድረኮችና ሚዲያዎች ላይ በመግለጽ ይታወቃሉ። በፍትሕ ጋዜጣ ፣ ፋክት መፅሔት ፣ ልዕልና ጋዜጣ ፣ አዲስ ታይምስ መፅሔትና እና በሌሎች የህትመት ሚዲያዎች ላይ የአርበኞችን ታሪክና ሌሎች ሀሳቦችን ሲፅፉ የቆዩ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በዩቲዩብ ሚዲያዎች በእንግድነት በመቅረብ አነጋጋሪ ቃለ መጠይቆችን ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ሲዳረጉና ሲፈቱ ቆይተዋል። የአሁን እስርም በግንቦት 10/2014 የ “ጥላቻ ንግግር በማሰራጨትና የእርስ በእርስ ግጭት በመቀስቀስ” ወንጀል ተጠርጥረው ነው።
በ2012 አ.ም. በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ መውጣቱ ይታወሳል።
በ2012 አ.ም. በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ መውጣቱ ይታወሳል።
አዋጁ በተራ ቁጥር 4 ስር “ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡” ይህን በማለት የጥላቻ ንግግር ስለመከልከሉ ያሰፈረ ሲሆን ፤ የጥላቻ ንግግር ያደረገ ማንኛውም ሰው እስከ ሁለት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 100 ሺ ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ ፣ እንዲሁም በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እንደሚሆንም አዋጁ አስቀምጧል።